ቀጥታ፡

የግብርና ምርታማነትን ወደተሻለ ምዕራፍ የሚያሸጋግር የፋይናንስ አቅርቦት ምኅዳር እየተፈጠረ ነው

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 14/2018 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያን የግብርና ምርታማነት ወደተሻለ ምዕራፍ የሚያሸጋግር የፋይናንስ አቅርቦት ምኅዳር እየተፈጠረ እንደሚገኝ የግብርና ሚኒስትር አዲሱ አረጋ ገለጹ።

የግብርና ሚኒስቴር ከክልሎችና ሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች የቢሮ ኃላፊዎችና በግብርና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ከተሰማሩ ባለኃብቶች ጋር በግብርና ኢንቨስትመንት አፈጻጸም ዙሪያ የምክክር መድረክ አካሂዷል።


 

በዚሁ ወቅት የግብርና ሚኒስትር አዲሱ አረጋ፤ የኢትዮጵያ ዘመናዊ የግብርና ምርታማነት በማስቀጠል የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የግል ባለሃብቱ ሚና ወሳኝ ነው ብለዋል።

አሁን ላይ በኢትዮጵያ 21 ሚሊየን ሔክታር የእርሻ መሬት እየለማ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በቀጣይም መታረስ የሚችል 38 ነጥብ 5 ሚሊየን ሄክታር መሬት ለማልማት የአነስተኛ ባለይዞታ አርሶ አደሮችንና ሰፋፊ የእርሻ ኢንቨስትመንት አቅምን ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ለዚህም አዳዲስ የፖሊሲ ማዕቀፎችን በማዘጋጀት የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሃብቶችን የእርሻ ኢንቨስትመንት የሚያበረታታ ምኅዳር እየተፈጠረ መሆኑን አስገንዝበዋል።

የእርሻ ኢንቨስትመንት የፋይናንስ ማነቆዎችን መፍትሔ ለመስጠት የግብርና ባንክ ማቋቋም የሚያስችል የመጨረሻ የዝግጅት ምዕራፍ ላይ መደረሱን አስታውቀዋል።

በቅርቡም በሙከራ ትግበራ ደረጃ በተለያዩ ወረዳዎች የአርሶ አደሮች የፋይናንስ ብድር አቅርቦት በይፋ እንደሚጀመር አንስተዋል።

በተጨማሪም የልማት አጋሮችና የፋይናንስ ተቋማት ለኢትዮጵያ የግብርና ሥርዓት መሻሻል የገንዘብ ብድር የሚያቀርቡበትን ምቹ ሁኔታ እየተፈጠረ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያን የግብርና ምርታማነት ወደተሻለ ምዕራፍ የሚያሸጋግር የፋይናንስ አቅርቦት ምኅዳር እየተፈጠረ እደሚገኝ አብራርተዋል።


 

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ሶፊያ ካሳ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የእርሻ ኢንቨስትመንት አልሚ ባለሃብቶች የሚቀርብላቸውን የገንዘብ ብድር ለታለመለት ዓላማ ማዋል እንደሚኖርባቸው አሳስበዋል።

ከተሳታፊዎች መካከል አቶ በለው ወንድም የእርሻ ኢንቨስትመንትን ለማሻሻል የሚደረገው የፋይናንስ አቅርቦት ምርታማነትን ለማሳደግ ጉልህ ጠቃሜታ አለው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም