የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንሳዊ መረጃዎች ለማሀበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች መሳለጥ ወሳኝ ደርሻ እየተወጡ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንሳዊ መረጃዎች ለማሀበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች መሳለጥ ወሳኝ ደርሻ እየተወጡ ነው
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 14/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንሳዊ መረጃዎች ለማሀበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች መሳለጥ ወሳኝ ደርሻ እየተወጡ እንደሚገኝ የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ፈጠነ ተሾመ ገለጹ።
የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ዓለምአቀፍ የሚቲዎሮሎጂ ቀንን በኢትዮጵያ ለ45ኛ ጊዜ "ዛሬን መመልከት፤ ነገን ለመጠበቅ" በሚል መሪ ሃሳብ አክብሯል።
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተርና በዓለም አቀፍ የሚቲዎሮሎጂ ድርጅት የአፍሪካ አህጉር ፅህፈት ቤት ፕሬዝዳንት ፈጠነ ተሾመ፤ የሚቲዎሮሎጂ መረጃ ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች መሳለጥ ቁልፍ ጉዳይ ነው ብለዋል።
የሚቲዎሮሎጂ መረጃ አገልግሎት አሰጣጥን የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ ተቋሙ በተለያዩ አካባቢዎች ለሚያከናውናቸው ስራዎች አስፈላጊ መሰረተ ልማቶች እንዲሟሉ እንደሚደረግ ገልጸዋል።
የባለሙያዎችን አቅም ማጠናከር እንዲሁም ዘመኑን የሚመጥኑ ቴክኖሎጂዎች ተግባራዊ መደረጋቸውን አንስተዋል።
ኢንስቲትዩቱ የሚያቀርባቸው የአየር ትንቢያ መረጃዎች በተደራጀ፣ ትክክለኛና ተደራሽ በሆነ መንገድ በስፋት ለልማት ስራዎች አገልግሎት ላይ እየዋሉ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ከአየር ንብረ ለውጥ ጋር ተያይዞ የሚመጡ አደጋዎችን መከላከል የሚያስችሉ ስራዎች ላይ ባለድርሻ አካላት ተገቢውን ትኩረት በመስጠት ሊሰሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ለ45ኛ ጊዜ የተከበረው ዓለም አቀፍ የሚቲዎሮሎጂ ቀን በቀጣይ በመስኩ የተሻሉ ስራዎችን ይበልጥ ለማጠናከርና ተደራሽነትን ለማስፋት አስቻይ ሁኔታ እንደሚፈጥርም ተናግረዋል።
በኢንስቲትዩት የዓለም አቀፍ ጣቢያዎች ኔትወርክ ፕሮጀክት አስተባባሪ ክንፈ ኃይለማሪያም በበኩላቸው፤ የተቋማትን ትብብር በማጠናከር የሚቲዎሮሎጂ መረጃዎችን በተለያዩ ቋንቋዎች ለማህበረሰቡ ተደራሽ እየተደረገ ነው ብለዋል።
ኢኒስቲትዩቱ ለመረጃ ሥርጭት ቴክኖሎጂ በመጠቀም ዕድገት አስመዝግቧል ያሉት ደግሞ በካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ ሳንታ በርበራ የምስራቅ አፍሪካ የአየር ጸባይ ሳይንቲስት ድሪባ ቆሪቻ(ዶ/ር) ናቸው።
የሚቲዎሮሎጂ መረጃዎች በሚፈለገው ልክ ጥቅም ላይ እንዲውሉ የዘርፉ ተዋናዮች የድርሻቸውን መወጣት እንዳለባቸው ተናግረዋል።