ቀጥታ፡

ሕዳሴ ግድብ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራትን የኢኮኖሚ ውህደት በማፋጠን ለጋራ ብልጽግና መሠረት እየጣለ ነው - ሚኒስትር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 14/2018(ኢዜአ)፦ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራትን የኢኮኖሚ ውህደት በማፋጠን ለጋራ ብልጽግና መሠረት እየጣለ እንደሚገኝ የውኃና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ(ዶ/ር) ገለጹ።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ጋር በመተባበር ''የሃይድሮ ዲፕሎማሲና ቀጣናዊ ትብብር ለዘላቂ ውኃና ኢነርጂ ልማትና አስተዳደር'' በሚል መሪ ሃሳብ መጋቢት 14 እና 15/2018 ዓ.ም ቀጣናዊ ጉባኤ በቢሾፍቱ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።


 

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ሃብታሙ ኢተፋ(ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት የዓባይ ተፋሰስ የጋራ ትብብር ለሀገራት ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ወሳኝ ነው።

የዓባይ ተፋሰስ ሀገራትም ቀጣናዊ የኃይልና የመሰረተ ልማት ትስስር አቅም በመገንባት የጋራ ብልጽግናን የሚያረጋግጥ ትብብር ማጠናከር እንደሚኖርባቸው ተናግረዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራትን የኢኮኖሚ ውህደት በማፋጠን ለጋራ ብልጽግና መሠረት እየጣለ መሆኑንም አስረድተዋል።


 

በቀጣይም የዓባይ ወንዝ ቀጣናዊ የጋራ የኢኮኖሚ ትስስርን ለማሳለጥ በአካባቢ ጥበቃና መሰል የልማት መስኮች በቁርጠኝነት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

የደቡብ ሱዳን ሪፐብሊክ የውኃና መስኖ ሚኒስትር ጀምስ ማዊች በበኩላቸው፤ የአየር ንብረት ለውጥ፣ የውሃና ኢነርጂ ፍላጎት በውሃ ሃብት ላይ ተፅዕኖ እያሳደረ ነው ብለዋል።

የድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን ፍትሐዊ የጋራ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ያስፈልጋል ያሉት ሚኒስትሩ፤ ለዚህም ደቡብ ሱዳን ለዘላቂ ቀጣናዊ ውሃ ሃብት አጠቃቀም ትብብር ቁርጠኛ ናት ብለዋል።

የዓባይ ተፋሰስ ሀገራት ህዝቦችን የጋራ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የትብብር አቅምን ማጎልበት ያስፈልጋል ያሉት ደግሞ የዑጋንዳ ሪፐብሊክ የውሃና አካባቢ ጥበቃ ሚኒስትር ዴኤታ ቢያትሪስ አቲም ናቸው።

የተፋሰሱ ሀገራትም በትብብር ላይ የተመሰረተ ቀጣናዊ ብልጽግናን ማረጋገጥ እንደሚገባ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በጉባዔው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውሃ፣ መስኖና ቆላማ አካባቢ ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አወቀ አምዛዬ(ዶ/ር)፣ የአፍሪካ ሀገራት የውሃ ሚኒስትሮች፣ የዘርፉ ተመራማሪዎችና ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም