ቀጥታ፡

ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ግልጽና ትክክለኛ በመሆን አርዓያነታቸውን ማሳየት ይጠበቅባቸዋል

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 14/2018 (ኢዜአ)፡- ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከማንኛውም ተቋም በበለጠ ግልጽና ትክክለኛ በመሆን አርዓያነታቸውን ማሳየት ይጠበቅባቸዋል ሲሉ የትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ገለጹ፡፡

የትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የአመራር አመዳደብ መመሪያ፣ የመንግስት ከፍተኛ ተቋማት የራስ ገዝነት ሽግግር መመሪያ፣ የራስ ገዝ የመንግስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የጥቅል በጀት ድጋፍ ደንብ ዙሪያ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፕሬዝዳንቶች እና የዘርፉ ተዋንያን ጋር ውይይት አካሂዷል፡፡

ሰነዶቹ በከፍተኛ ትምህርት አዋጅ ቁጥር 1151/2011 በተሰጠው ስልጣን መሰረት በሙያቸው የሰለጠኑ ብቃትና ችሎታ ያላቸው የትምህርት አመራር አባላትን ወደ ሥራ ማምጣት የሚያስችሉ መሆናቸው ተገልጿል፡፡
 

የትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ መንግሥት የትምህር ተቋማት ግልጽነትና ተጠያቂነትን በማስፈን የትምህርት ጥራትና ተደራሽነት ማረጋገጥ የሚያስችሉ የሪፎርም ሥራዎችን እያከናወነ ነው፡፡

አዋጆችን ለማስፈጸም የተዘጋጁት ደንብና መመሪያዎች ተቋማቱ የሚሰጣቸውን ሀብት በአግባቡ ማስተዳደርና ለታለመለት ዓላማ እንዲያውሉ ያስችላሉም ብለዋል።

ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከማንኛውም ተቋም በበለጠ ግልጽ፣ ተዓማኒና እውነተኛ በመሆን አርዓያነታቸውን ማሳየት አለባቸው ሲሉም ተናግረዋል፡፡

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የአመራር አመዳደብ መመሪያ በተቋማት ላይ የነበረውን ስር የሰደደና ልማዳዊ አሰራሮቸን የሚያስቀር መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ኮራ ጡሽኔ በበኩላቸው፤ የራስ ገዝ የመንግሥት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጥቅል የበጀት ደንብ ተቋማት የተመደበላቸውን በጀት በአግባቡ መጠቀምና የፋይናንስ ምንጫቸውን ማስፋት እንደሚያስችላቸው ገልጸዋል፡፡

ከዚህም ባለፈ የትምህርት ሚኒስቴር የሀገርን ሀብት በፍትሐዊነት በመመደብ በዩኒቨርሲቲዎች ተጠያቂነትን ያሰፍናል ብለዋል፡፡

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የአመራር አመዳደብ መመሪያ ተቋማቱን ወደ ራስ ገዝነት የሚያሸጋገር ግልፅ አሰራር መሆኑን ጠቅሰው፤ የአካዳሚክ ነፃነትንም እንደሚያረጋገጥ ተናግረዋል፡፡

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፕሬዝዳንቶችና ምክትል ፕሬዝዳንቶች የሚመረጡበት መመሪያ ዕውቀትና ልምድን መሰረት ያደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ደንብና መመሪያዎቹ ጥድፊያ የተሞላበትና ግልፅነት የጎደለው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አመራሮች አሰያየምን ያስቀራሉም ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም