አዳዲስና የተከለሱ 79 የኢትዮጵያ ደረጃዎች ጸድቀዋል - ኢዜአ አማርኛ
አዳዲስና የተከለሱ 79 የኢትዮጵያ ደረጃዎች ጸድቀዋል
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 14/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢኒስቲትዩት አዳዲስና የተከለሱ 79 ደረጃዎች መጽደቃቸውን ገለጸ።
አኒስቲትዩቱ በሰጠው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ የደረጃዎች ቦርድ ካጸደቃቸው ደረጃዎች መካከል 56 አዳዲስ ሲሆኑ፤ 23 ደግሞ የተከለሱ ናቸው።
የደረጃዎች ቦርድ ደረጃዎችን ያጸደቀው በምግብና ግብርና ዘርፍ፣ በመሰረታዊና አጠቃላይ ዘርፍ እንዲሁም በኤሌክትሮ መካኒካል ዘርፍ መሆኑ ተመልክቷል።
የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢኒስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር መሰረት በቀለ(ዶ/ር) በሰጡት መግለጫ፤ ቦርዱ ካጸደቃቸው ደረጃዎች መካከል አስገዳጅ የህጻናት ምግብ ደረጃዎች፣ የተከለሱ የህጻናት ምግብ መፈተሻዎች፣ አስገዳጅ የማርና ማር ውጤቶች ደረጃዎች፣ የማርና የማር ውጤት መፈተሻዎች ይገኙበታል ብለዋል።
የሳይበር ደህንነት አስገዳጅ ደረጃዎች እንዲሁም ሌሎች ደረጃዎች መጽደቃቸውንም ጨምረው ጠቅሰዋል።
የህጻናት ወተትን ጨምሮ ከውጭ የሚገቡ ምርቶች ጥራትና ደህንነትን በተገቢው መልኩ ለመፈተሽ፣ ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶች ጥራትና ተወዳዳሪነት በማሳደግ በኩል የደረጃዎቹ መጽደቅ ዘርፈ ብዙ ፋይዳ እንዳለው አብራርተዋል።
በአሁኑ ወቅት እንደ ሀገር ከ12ሺህ በላይ ደረጃዎች መኖራቸውን ጠቁመው፤ በደረጃዎች ቦርድ የጸደቁት ሥራ ላይ መዋል ተጨማሪ አቅም ይፈጥራሉ ብለዋል።
የአገልግሎት ጥራትን ማሳደግ ሌላው ዓላማ መሆኑን ጠቁመው፤ እንደ ሀገር ፋይዳው ከፍ ያለ መሆኑንም አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢኒስቲትዩት የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ ብሩክ ሀብቴ በበኩላቸው፤ በቦርዱ ከጸደቁት 79 ደረጃዎች ውስጥ 28ቱ አስገዳጅ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በምግብና ግብርና ዘርፍ ስድስት የተከለሱ አስገዳጅ የግብርና ማዳበሪያ ደረጃዎች፣ ሁለት አስገዳጅ የህጻናት ምግብ ደረጃዎች፣ ሰባት የተከለሱ የህጻናት ምግብ መፈተሻዎች፣ አንድ የማርና ማር ውጤት ምርቶች አስገዳጅ ደረጃ፣ ሁለት አዲስ የማርና ማር ውጤት መፈተሻዎች ከጸደቁት መካከል እንደሚገኙበት አብራርተዋል።
በተመሳሳይም ሁለት አዲስ አጠቃላይ የምግብ ምርቶች አስገዳጅ ደረጃዎች፣ ሦስት አዲስ እና ዘጠኝ የተከለሱ በድምሩ 12 መፈተሻዎች መጽደቃቸውንም አንስተዋል።
በመሰረታዊና አጠቃላይ ዘርፍ ደግሞ ሦስት ጂኦግራፊያዊ መረጃ አስገዳጅ ደረጃዎች፣ አምስት አዲስ የሳይበር ደህንነት አስገዳጅ ደረጃዎች፣ 30 አዲስ የሳይበር ደህንነት መፈተሻዎች፣ ሁለት አዲስ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎትና አስተዳደር ሥርዓት አስገዳጅ ደረጃዎች በቦርዱ መጽደቃቸውን ተናግረዋል።
በኤሌክትሮ መካኒካል ዘርፍ ደግሞ ስድስት አዲስ የትራንስፖርት አስገዳጅ ደረጃዎችና አንድ አዲስ የባቡር መንገድ የምህንድስና አስገዳጅ ደረጃ እንደሚገኙበትም አስረድተዋል።