የክልሉ ሕዝብ የምርጫ ካርድ በመውሰድ ዴሞክራሲያዊ መብቱን በተግባር ማረጋገጥ አለበት - ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ - ኢዜአ አማርኛ
የክልሉ ሕዝብ የምርጫ ካርድ በመውሰድ ዴሞክራሲያዊ መብቱን በተግባር ማረጋገጥ አለበት - ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 14/2018 (ኢዜአ)፦ የሀረሪ ክልል ሕዝብ የምርጫ ካርድ በመውሰድ ዴሞክራሲያዊ መብቱን በተግባር ማረጋገጥ አለበት ሲሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ተናገሩ።
ርዕሰ መስተዳድሩ እንደገለጹት ሕዝቡ የምርጫ ካርድ በመውሰድ የተጀመረውን የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ለማጠናከር ሚናውን መወጣት አለበት።
በክልሉ ለምርጫው ሂደት ስኬታማነት ምቹ ሁኔታዎችን የመፍጠር ሥራ በተቀናጀ መልኩ እየተከናወነ መሆኑንም ተናግረዋል።
መንግሥት ነፃ፣ ፍትሐዊና ተዓማኒ ምርጫ ለማካሄድ ሁለንተናዊ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ጠቅሰው፤ ምርጫው ስኬታማ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ሕዝቡ ከወዲሁ የምርጫ ካርድ መውሰድ እንዳለበት አንስተዋል።
ከክልሉ ውጪ የሚኖሩ የሀረሪ ብሔረሰብ ተወላጆች በሚመርጡባቸው የምርጫ ጣቢያዎች አዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር፣ በኦሮሚያ ክልል (አዳማ፣ ጭሮ፣ ኮምቦልቻ ፣ ጉርሱም፣ ፈዲስ፣ ደደር እና ሃሮማያ)፣ ድሬዳዋ ከተማ መስተዳድር ፣ እና በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ በተቀመጠው የጊዜ ገደብ የምርጫ ካርድ በመውሰድ ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን በአግባቡ እንዲጠቀሙም መልዕክት አስተላልፈዋል።
በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች ምርጫው በታቀደለት የጊዜ ገደብ ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ አሳስበዋል።