ቀጥታ፡

ሴቶች ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ እያደረጉት ያለውን ተሳትፎ ለማሳደግ ትኩረት ተደርጓል

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 14/2018 (ኢዜአ)፦ ሴቶች ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ እያደረጉት ያለውን ተሳትፎ ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ሀይሉ አዱኛ ገለጹ።

50ኛ ዙር የጉሚ በለል ውይይት መድረክ “በዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ የ50+ ሚና” በሚል መሪ ሃሳብ በኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጽሕፈት ቤት ተካሂዷል።


 

በስነ-ስርዓቱ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ሀይሉ አዱኛ እንደገለጹት ለሁሉም ዜጎቿ የምትመች ሀገር ለመገንባት የተጀመረው የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ተጠናክሮ ይቀጥላል።

ህዝቡ የስልጣን ባለቤት መሆኑን የሚያረጋግጥ ስርዓትን ለመዘርጋት የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሚገኙ አንስተው፤ ያለፉ የፖለቲካ ችግሮችን በሀገራዊ ምክክር ለመፍታት የተጀመረው ጉዞ አዲስ ምዕራፍ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይም ሴቶች ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታው እያደረጉ ያለውን ተሳትፎ ለማሳደግ ትኩረት መደረጉን ተናግረዋል።


 

የኦሮሚያ ሴቶችና ህጻናት ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ መብራት ባጫ እንዳሉት ሴቶች ያለባቸውን ድርብ ኃላፊነት በብቃት ከመወጣት ባለፈ በዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ አበርክቷቸው የላቀ ነው።

የለውጡ መንግስት የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎ በማሳደግ አመርቂ ስኬት ማስመዝገብ መቻሉንም ተናግረዋል።

በኮተቤ ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪ ፋኖሴ መንግስቱ (ዶ/ር) ባቀረቡት የመወያያ ጥናት በሀገሪቱ የሴቶች ተሳትፎ እያደገ በመምጣቱ በወረዳ፣ በዞን፣ በከንቲባ፣ በሚኒስትርነትና በፓርቲም ደረጃ በተሻለ ሁኔታ በመምራት ከፍተኛ ውጤት እየተመዘገበ ነው ብለዋል።


 

አክለውም በማህበራዊና በኢኮኖሚያዊ ዘርፍ የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ ጠንካራ ስራ ሊሰራ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።‎

7ኛው ጠቅላላ ምርጫን ለማሳካት የሁሉም አካላት ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑ ቢታመንም የሴቶች የተደራጀ ተሳትፎ ሚናው የጎላ መሆኑንም አመልክተዋል።

ከተሳታፊዎች መካከል ከአዲስ አበባ አመራር አካዳሚ የመጡ አቶ ሰለሞን ተፈራ፤ በአገሪቱ በሁለንተናዊ እድገት መስክ ለተገኘው ድል የሴቶች ተሳትፎ ወሳኝ ሚና እንደነበረው ገልጸዋል።

በቀጣይም ሴቶች በጠቅላላ ምርጫውና በሀገራዊ ምክክሩ ያላቸውን የነቃ ተሳትፎ ሊያጠናክሩ ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም