ቀጥታ፡

በክልሉ የከርሰ ምድር ውሃን በማበልጸግ ለመጠጥ ውሃ አቅርቦት የማዋል ተግባር በትኩረት እየተከናወነ ነው

ባህር ዳር፤ መጋቢት 14/2018(ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል የከርሰ ምድር ውሃን በማበልጸግና በማልማት ለመጠጥ ውሃ አቅርቦት የማዋል ተግባር በትኩረት እየተከናወነ መሆኑን የክልሉ ውሃና ኢነርጂ ቢሮ አስታወቀ።

ቢሮው "ውሃና ስርዓተ ጾታ" በሚል መሪ ሃሳብ በአለም አቀፍ ደረጃ ለ34ኛ ጊዜ የሚከበረውን የውሃ ቀን በባህር ዳር ከተማ በውይይት አክብሯል።

በቢሮ ሃላፊ ደረጃ የክልሉ ውሃና ኢነርጂ ቢሮ ዋና አማካሪ ወልደትንሳኤ መኮንን(ዶ/ር) በመድረኩ እንደገለጹት፤ በክልሉ የከርሰ ምድር ውሃን በማበልጸግ የንጹህ መጠጥ ውሃ ሽፋንን ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ ነው።

በተያዘው በጀት ዓመትም 2ሺህ 445 አነስተኛ የውሃ ተቋማትን ለመገንባት በተደረገ ጥረት እስካሁን 603 የሚሆኑትን በማጠናቀቅ ለአገልግሎት ማብቃት መቻሉን ገልጸዋል።

ቀሪዎቹን በተያዘላቸው ጊዜ ለማጠናቀቅ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመው ህብረተሰቡም እስካሁን 173 ሚሊየን ብር የሚገመት አስተዋፅኦ በጥሬ ገንዘብና በጉልበት ማድረጉን ተናግረዋል።

ቢሮው የዘላቂ ልማት ግቦችን መሰረት በማድረግ የንጹህ መጠጥ ውሃና የኢነርጂ አቅርቦትን ተደራሽ ለማድረግ እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመው ህብረተሰቡም ተቋማቱን በባለቤትነት እንዲጠብቅ አስገንዝበዋል።

የደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ መምህር ዋለልኝ ካሴ በመድረኩ ባቀረቡት ጽሁፍ ያለውን የውሃ ሃብት ክምችት፣ ጥራትና ለምን አገልግሎት እንደሚውል ቀድሞ በመለየት ውጤታማ የማልማት ስራ ለማከናወን አርቲፊሻል ኢንተለጀንስን መጠቀም እንደሚገባ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም