የሀላባ ቁሊቶ ስታዲዮም ግንባታ የአካባቢውን የስፖርት እንቅስቃሴ እያነቃቃ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የሀላባ ቁሊቶ ስታዲዮም ግንባታ የአካባቢውን የስፖርት እንቅስቃሴ እያነቃቃ ነው
ሀላባ ቁሊቶ፤ መጋቢት 14/2018 (ኢዜአ) :- የሀላባ ቁሊቶ ስታዲዮም ግንባታ የአካባቢውን የስፖርት እንቅስቃሴ እያነቃቃ መሆኑ ተገለጸ፡፡
በእግር ኳሱ ኢትዮጵያን የሚወክሉ ስፖርተኞች መፍለቂያ በሆነው የሃላባ ዞን የስፖርት መሰረተ ልማት አለመኖር በርካታ ብቁ ስፖርተኞችን ለማፍራት ተግዳሮት ሆኖ ቆይቷል።
አሁን ላይ ለዘርፉ በተሰጠው ትኩረት ደረጃውን የጠበቀ ስታዲዮም ግንባታ መጀመሩ ለአካባቢው የስፖርት እንቅስቃሴ መነቃቃት መፍጠሩን አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ነዋሪዎች ተናግረዋል።
ከነዋሪዎቹ መካከል አቶ ንጋቱ መለሰ እና አቶ ሳባቶ አህመድ እንደገለጹት ሀላባ ዞን በእግር ኳስ ስፖርት ትልቅ ስም የነበረው ቢሆንም በትኩረት ማነስና በመሰረተ ልማት እጦት ማደግ በሚገባውና ባለው አቅም ልክ ማደግ አልቻለም።
በግንባታ ሂደት አገልግሎት መስጠት የጀመረው የሀላባ ቁሊቶ ስታዲዮም በዘርፉ የተፈጠረውን መቀዛቀዝ በመቀየር አካባቢውን የስፖርት ልማት ዘርፍ በከፍተኛ ሁኔታ ማነቃቃቱን ተናግረዋል።
የስታዲዮሙ ግንባታ የእግር ኳስ አፍቃሪውን ዳግም ወደ ሜዳ የሚመልስና ሀገርን የሚወክሉ ስፖርተኞች እንዲፈልቁ የሚያደርግ ነው ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ “ለ” ቡድኖች ጨዋታቸውን በስታዲዮሙ እያደረጉ ሲሆን አስተያየታቸውን የሰጡት የኤልቴክ እግር ኳስ ቡድን አሰልጣኝ ይገረም ኤሊያስ በጥሩ ሜዳ መጫወት ውጤትን ይወስናል ብለዋል።
ለስፖርት መሰረተ ልማት በተሰጠው ትኩረት ደረጃቸውን የጠበቁ ስታዲዮሞች መገንባት ለሀገሪቱ የእግር ኳስ ስፖርት ዕድገት ሚናው የጎላ መሆኑን ጠቁመዋል።
የሃላባ ዞን ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ታገል ጌታቸው በበኩላቸው፤ በህዝብ ተሳትፎ ግንባታው የተጀመረው የሀላባ ስታዲዮም የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን ገልጸዋል፡፡
ሰው ሰራሽ የመጫወቻ ሜዳ፣ የተመልካች መቀመጫ፣ የፍሳሽ ማስወገጃና ሌሎችም በመጀመሪያው ምእራፍ ግንባታ መጠናቀቃቸውን የገለጹት ሃላፊው በስፖርት ዘርፉ ከፍተኛ መነቃቃት ተፈጥሯል ብለዋል፡፡
የግንባታው ሁለተኛ ምዕራፍ አካል የሆኑት የመብራትና ዓለም አቀፍ መመዘኛ ያሟላ የክቡር ትሪቡን ግንባታ እየተካሄደ መሆኑን ጠቅሰዋል።
አካባቢው በእግር ኳስ ክህሎት የዳበረና የላቀ ብቃት ያላቸው ተተኪ ስፖርተኞች የሚፈሩበት እንደሆነ ጠቅሰው ሜዳው አገልግሎት መስጠት መጀመሩ ብቁ ስፖርተኞችን ለማፍራት እየተደረገ ያለውን ጥረት እንደሚደግፍም አመልክተዋል።
ግንባታው በሁለት ምዕራፍ እየተከናወነ የሚገኘው ስታዲዮሙ የካፍ ስታንዳርድን ባሟላ መልኩ እየተገነባ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን ሲጠናቀቅም ክልላዊም፣ ሀገር አቀፍና ሌሎች ውድድሮችን ለማስተናገድ እንደሚያስችልም ተናግረዋል።