ቀጥታ፡

በጋምቤላ ክልል በግብርና፣ በማዕድንና በሌሎች የልማት ዘርፎች ውጤታማ ስራዎች ተከናውነዋል

ጋምቤላ፤ መጋቢት 14/2018 (ኢዜአ)፦ በጋምቤላ ክልል በግብርና በማዕድንና በሌሎች የልማት ዘርፎች ውጤታማ ስራዎች መከናወናቸውን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዓለሚቱ ኡሞድ ገለፁ።

‎የክልሉ ምክር ቤት ዛሬ ባካሔደው መደበኛ ጉባኤ የክልሉን የግማሽ በጀት ዓመት የልማትና የመልካም አስተዳደር እቅድ አፈፃፀም ሪፖርት አድምጧል።

‎ርዕሰ መስተዳድሯ የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርቱን ለምክር ቤቱ ባቀረቡበት ወቅት እንዳሉት በክልሉ በሰላም ግንባታ፣ በግብርና፣ በማዕድን፣ በገቢና በሌሎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ውጤታማ ስራዎች ተከናውነዋል ብለዋል።

‎በክልሉ ተከስቶ የነበረውን የፀጥታ ችግር ለመፍታት በሕዝቡና በፀጥታ አካሉ የተደረገው የተቀናጀት ጥረት የተረጋጋ ሰላም ማምጣት አስችሏል ነው ያሉት።

‎‎‎በ2017/18 የምርት ዘመን ከ186 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በማልማት ከ6 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መሰብሰብ መቻሉንም ገልፀዋል።

ይህም ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ኩንታል ብልጫ እንዳለው በሪፖርቱ አመላክተዋል።

‎‎በማዕድን ልማት ዘርፉም በመጀመሪዎቹ ስድስት ወራት 3 ሺህ ኪሎ ግራም ወርቅ ወደ ብሔራዊ ባንክ ለማስገባት ታቅዶ 3 ሺህ 860 ኪሎ ግራም መግባቱን ጠቅሰዋል።

‎አፈፃፀሙ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ1 ሺህ 057 ኪሎ ግራም ብልጫ እንዳለው ነው የገለጹት።

‎‎የክልሉን የገቢ አቅም ለማሳደግ በተከናወኑ ተግባራትም በግማሽ ዓመቱ ከ2 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን በሪፖርቱ አመላክቷል።

በተጨማሪም በትምህርት፣ በጤና፣ በንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት፣ በመሠረተ ልማት ዝርጋታ፣ በስራ ዕድል ፈጠራና በሌሎች የልማት መስኮች አበረታች ስራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም