ሀገራዊ ምክክር በእያንዳንዳችን ሕይወት ውስጥ ምን ፋይዳ አለው? - ኢዜአ አማርኛ
ሀገራዊ ምክክር በእያንዳንዳችን ሕይወት ውስጥ ምን ፋይዳ አለው?
በሀገራችን ኢትዮጵያ እየተተገበረ የሚገኘው የሀገራዊ ምክክር ሂደት በተለያዩ ባለድርሻ አካላት መካከል ላለመግባባታችን ምክንያት የሆኑ እጅግ መሰረታዊ ሀገራዊ ጉዳዮችን ነቅሶ በማውጣት ምክክር እንዲደረግባቸው በመስራት ላይ ይገኛል፡፡
የሥነ-ምክክር መዛግብት የሚያስረዱት ሀገራዊ ምክክር በአንድ ሀገር ውስጥ የሚገኙ ዜጎች ተጠቃሚ የሚሆኑባቸውን ሀገራዊ ጉዳዮች በንግግር እንዲስተካከሉ እንደሚረዳ ነው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ያስታወቀው፡፡
ከዚህ አኳያ እኛ ኢትዮጵያውያን በሀገራችን ኢትዮጵያ እየተከናወነ የሚገኘው የሀገራዊ ምክክር ሂደት በግለሰብ ደረጃ እንዴት ተጠቃሚ እንደሚያደርገን የሚከተሉት ሃሳቦች ከብዙ በጥቂቱ ያስረዳሉ፡፡
በነፃነት የመንቀሳቀስ መብት፡ ግጭቶች በንግግር የተፈቱበት ዓውድ ዜጎች ተገማች የሆነ ሕይወትን እንዲመሩ ያስችላቸዋል፡፡ ይህም ዜጎች በተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች ያለ ስጋት ለተለያዩ ዓላማዎች እንዲንቀሳቀሱ ትልቅ ነፃነትን ያጎናፅፋቸዋል፡፡
የሥራ ዕድሎችን ማስፋት፡ በንግግር መፈታት የሚገባቸው ግጭቶች እዚህም እዚያም መስተዋላቸው ትልልቅ የሥራ ዕድሎችን ሊፈጥሩ የሚችሉ የኢንቨስትመንት መስኮችን እንዲከስሙ አድርጓል፡፡ ይህም በሀገራችን ሙዓለ ንዋይ የሰለጠነ እጅግ ትኩስ እና አምራች የሰው ኃይል እውቀቱንና ልምዱን ለሀገሩ እንዳያበርክት በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡
የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት መጎልበት፡ ከሀገራዊ ምክክር ሂደት ተጠባቂ ውጤቶች እና ምክረ-ሀሳቦች አንዱ የተለያዩ ተቋማት የደንበኛ አያያዝ ጉዳዮችን ጨምሮ የተለያዩ ጉዳዮችን እንዲያሻሽሉ ማድረግ ነው፡፡ ይህም ዜጎች በሀገራቸው ተቋሞች ላይ ባለቤትነትን በማዳበር ለጋራ ችግሮቻቸው የጋራ መፍትሔዎችን እንዲያበጁ መንገድ ይከፍታል፡፡
የፀጥታ ሥጋትን መቀነስ፡ ዜጎች በሀገራቸው ኢትዮጵያ ውስጥ በሚፈጠሩ ፖለቲካዊ ውጥንቅጦች የፀጥታ ሥጋት ሰለባ ሆነዋል፡፡ የሀገራዊ ምክክር ሂደቱም ዜጎች በዕለት ተዕለት ህይወታቸው የሚገጥማቸውን የፀጥታ ስጋቶችን ከሥር መሰረቱ ለመፍታት በመነጋገር የተለያዩ የመፍትሔ ሀሳቦች እንዲመነጩ ያስችላል፡፡
የሥነ-ልቦናዊ ጫናዎችን መቀነስ፡ ግጭቶች በባህሪያቸው ላልተፈለገ የሥነ-ልቦና ጠባሳ እና ጫና ይዳርጋሉ፡፡ በግጭት ዓውድ ውስጥ የሚኖሩም ሆነ ግጭት በሌለበት የሀገራችን አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎች የዚህ ገፈት ቀማሽ መሆናቸው ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ባሉን የሃሳብ ልዩነቶች ዙሪያ በግልፅ እና በእውነት ለመነጋገር መፍቀዳችን መሰል ችግሮቻችን እንዲቀረፉ በእጅጉ ይረዳናል ሲልም ኮሚሽኑ ገልጿል፡፡