የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ሊጠናከር ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ሊጠናከር ይገባል
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 14/2018(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ግብርናን ወደ ላቀ ደረጃ በማሸጋገር የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ሊጠናከር እንደሚገባ የግብርና ሚኒስትር አዲሱ አረጋ ገለጹ።
የግብርና ሚኒስቴር ከክልሎችና ሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች የቢሮ ኃላፊዎችና በግብርና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ከተሰማሩ ባለኃብቶች ጋር በግብርና ኢንቨስትመንት አፈጻጸም ዙሪያ ውይይት እያካሄደ ነው።
የግብርና ሚኒስትር አዲሱ አረጋ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ በግብርናው ዘርፍ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ፣ ተኪ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ማምረት፣ ወጪ ምርቶችን በአይነትም በጥራትም የማሳደግ ግብ ተይዞ ርብርብ እየተደረገ ይገኛል።
ለኢንዱስትሪዎች ግብዓት የሚሆኑ ምርቶችን ማምረት እንዲሁም በግብርናው ዘርፍ የሥራ ዕድል ፈጠራ አቅም ማሳደግ ሌላው ግብ መሆኑንም አብራርተዋል።
ግቦቹን በውጤታማነት ለመተግበር መንግሥት የፖሊሲ እንዲሁም ስትራቴጂዎችና ሕጎች ሥራ ላይ በማዋል አስቻይ ሁኔታዎችን እየፈጠረ ይገኛል ብለዋል።
በዚህም በእርሻ ኢንቨስትመንት ዘርፍ በርካታ ስኬቶች መመዝገባቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል።
የምግብ ዋስትና ማረጋገጥን ጨምሮ በግብርናው ዘርፍ የተያዙ ሀገራዊ ውጥኖችን ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የግሉ ዘርፍ ወሳኝ ሚና እንዳለው ጠቁመው በዚህ ረገድ የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ሊጠናከር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ያለንን የግብርና አቅም አሟጦ በመጠቀም የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የእርሻ ኢንቨስትመንት ዘርፉን የሚያነቃቁ ልዩ ልዩ እርምጃዎች እየተወሰዱ መሆናቸውንም አመልክተዋል።
የውይይቱ ዋና ዓላማም የሰፋፊ የእርሻ ልማት አፈጻጸምን በመገምገም የቀጣይ አቅጣጫዎችን ለማስቀመጥ መሆኑን አስታውቀዋል።
ከውይይቱ ጎን ለጎን ለምግብ ዋስትና መረጋገጥ አዎንታዊ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት የታመነበት ብሄራዊ የማሽላ ፍላግሺፕ ፕሮግራም ይፋ እንደሚደረግ ተገልጿል።