ቀጥታ፡

ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚሰጣቸውን ሀብት ለታለመለት ዓላማ ማዋል የሚያስችሉ ደንቦችና መመሪያዎች ተዘጋጅተዋል 

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 14/2018 (ኢዜአ)፦የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚሰጣቸውን ሀብት በአግባቡ ማስተዳደርና ለታለመለት ዓላማ ማዋል የሚያስችሉ ደንቦችና መመሪያዎች መዘጋጀታቸውን የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ኮራ ጡሽኔ ገለጹ።

ደንብና መመሪያዎቹ ጥድፊያ የተሞላበትና ግልፅነት የጎደለው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አመራሮች አሰያየምን ማስቀረት ይችላሉም ተብሏል።

የትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የአመራር አመዳደብ መመሪያ፣ የመንግስት የከፍተኛ ተቋማት የራስ ገዝነት ሽግግር መመሪያ፣ የራስገዝ የመንግስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የጥቅል በጀት ድጋፍ ደንብ ዙሪያ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፕሬዝዳንቶች እና የዘርፉ ተዋንያን ጋር የውይይት መድረክ አዘጋጅቷል።

የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ኮራ ጡሽኔ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤መንግሥት የትምህርት ጥራትና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ወጥ የሆነ የአሰራር ሥርዓት ማስፈን የሚያስችል ሪፎርም አድርጓል።

ይህም ትምህርት ሚኒስቴር በከፍተኛ ትምህርት አዋጅ ቁጥር 1151/2011 በተሰጠው ስልጣን መሰረት በሙያቸው የሰለጠኑ ብቃትና ችሎታ ያላቸው የትምህርት አመራሮችን ወደ ሥራ ማምጣት የሚያስችል አሰራር መሆኑን ገልጸዋል።

ደንብና መመሪያዎቹ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚሰጣቸውን ሀብት በአግባቡ ማስተዳደርና ለታለመለት ዓላማ ማዋል ያስችላሉ ብለዋል።

ለመንግሥት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ወደ ራስገዝነት መሸጋገር የሚያስችል ግልፅ አሰራር መሆኑን ጠቅሰው፤ የአካዳሚክ ነፃነትን የሚያረጋግጥ መሆኑንም ገልጸዋል።

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፕሬዝዳንቶችና ምክትል ፕሬዝዳንቶች የሚመረጡበት መመሪያ ረጅም ጊዜ የሚወስድ ዕውቀትና ልምድን መሰረት ያደረገ ሰነድ መሆኑንም ተናግረዋል።

ደንብና መመሪያዎቹ ጥድፊያ የተሞላበትና ግልፅነት የጎደለው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አመራሮች አሰያየምን እንደሚያስቀሩ ገልጸዋል።

የራስገዝ የመንግሥት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጥቅል የበጀት ደንብ ተቋማት የተመደበላቸውን በጀት በአግባቡ መጠቀምና የፋይናንስ ምንጫቸውን እንዲያሰፉ እድል ይሰጣል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም