በጋሞ ዞን ኃይል ለተቋረጠባቸው አካባቢዎች ኃይል እንዲያገኙ እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በጋሞ ዞን ኃይል ለተቋረጠባቸው አካባቢዎች ኃይል እንዲያገኙ እየተደረገ ነው
አዲስ አበባ፤መጋቢት 14/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋሞ ዞን በደረሰው የተፈጥሮ አደጋ ኃይል ተቋርጦባቸው ለነበሩ አካባቢዎች ጊዜያዊ መስመር በመዘርጋት ኃይል እንዲያገኙ እያደረገ መሆኑን አስታወቀ፡፡
የአገልግሎቱ የአርባ ምንጭ ሪጅን በዞኑ በደረሰው የመሬት መንሸራተትና የጎርፍ አደጋ በአርባምንጭ ከተማ ብቻ 70 ምሰሶዎች፣ከ4 ኪ.ሜ በላይ የመካከለኛ መስመር ውድመት እና 4 የኤ.ኤም. አይ ቆጣሪዎች በጎርፍ መወሰዳቸውን ገልጿል።
በአርባምንጭ ዙርያ በገረሴ፣ ከንባ፣ ጨንቻና ምዕራብ አባያ ወረዳዎች በድምሩ ከ150 በላይ ምሰሶዎች እንዲሁም 10 ኪ.ሜ የመካከለኛ መስመር ውድመት መድረሱን አመልክቷል።
በተጨማሪም በአርባ ምንጭ ከተማ ቁጥር አንድ ማዕከል ግምጃ ቤት አዲስ ኃይል ጠያቂ ደንበኞችን ተጠቃሚ ለማድረግ የተቀመጡ 155 ምሰሶዎች በጎርፍ መወሰዳቸውንም ነው ያስታወቀው።
የአርባ ምንጭ ሪጅን የአገልግሎት መስጫ ማዕከላት የቴክኒክ ሠራተኞችና የሪጅኑ ሰራተኞች በመረባረብ የመልሶ ግንባታ ስራዎችን እያከናወኑ እንደሚገኝ ተገልጿል።
ሪጅኑ በዞኑ አደጋው በደረሰባቸው አካባቢዎች ለነበሩ የጤና ተቋማት፣ ትምህርት ቤቶች፣ የመስተዳድር ቢሮዎች እና ሌሎችም ቁልፍ ደንበኞች ኃይል ለመስጠት ከፍተኛ ርብርብ እያደረገ እንደሆነም ነው በመረጃው ያመለከተው።
ቤታቸው በጎርፍ ከተወሰደባቸው ደንበኞች ውጪ ያሉት የአርባምንጭ፣ የገረሴ፣ የከንባ፣ የጨንቻና የምዕራብ አባያ ነዋሪዎች ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ የኤሌክትሪክ ኃይል እንዲያገኙ መደረጉን ጠቁሟል።