አሜሪካ በዓለም አትሌቲክስ የቤት ውስጥ ሻምፒዮና አንደኛ ደረጃን ይዛ አጠናቀቀች - ኢዜአ አማርኛ
አሜሪካ በዓለም አትሌቲክስ የቤት ውስጥ ሻምፒዮና አንደኛ ደረጃን ይዛ አጠናቀቀች
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 14/2018 (ኢዜአ)፦ አሜሪካ በ21ኛው የዓለም አትሌቲክስ የቤት ውስጥ ሻምፒዮና 18 ሜዳሊያዎችን በማግኘት አሸናፊ ሆናለች።
በፖላንድ ቶሩን ከተማ ከመጋቢት 11 ቀን 2018 ዓ.ም አንስቶ ሲካሄድ የቆየው ሻምፒዮና ትናንት ማምሻውን ተጠናቋል።
በሻምፒዮናው ከ118 ሀገራት የተወጣጡ 674 አትሌቶች ተሳትፈዋል።
አሜሪካ በአምስት ወርቅ፣ በሰባት ብር እና ስድስት ነሐስ በአጠቃላይ 18 ሜዳሊያዎችን በማግኘት ውድድሩን በአንደኝነት አጠናቃለች።
ታላቋ ብሪታኒያ (ሰሜን አየርላንድን ጨምሮ) በአራት ወርቅ ሁለተኛ ሆና ጨርሳለች።
ጣልያን በሶስት የወርቅ እና ሁለት የብር በድምሩ አምስት ሜዳሊያዎችን በማግኘት ሶስተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።
ዩክሬን እና ፖርቹጋል በተመሳሳይ ሁለት የወርቅ እና አንድ ብር በድምሩ ሶስት ሜዳሊያዎችን አግኝተው አራተኛ ወጥተዋል።
በውድድሩ ላይ ከተሳተፉ አፍሪካ ሀገራት የወርቅ ሜዳሊያ ያገኘ ሀገር የለም።
ሴኔጋል እና አልጄሪያ በተመሳሳይ አንድ አንድ የነሐስ ሜዳሊያ በማግኘት 24ኛ ደረጃን ይዘው ውድድራቸውን አጠናቀዋል።
በሻምፒዮናው ላይ ከተሳተፉ 118 ሀገራት መካከል ሜዳሊያ ያገኙት 32ቱ ብቻ ናቸው።
በሻምፒዮናው በስድስት አትሌቶች የተወከለችው ኢትዮጵያ ምንም ሜዳሊያ ሳታገኝ አጠናቃለች።