አዲስ አበባ ከተማ በሊጉ ሶስተኛ ድሉን አስመዘገበ - ኢዜአ አማርኛ
አዲስ አበባ ከተማ በሊጉ ሶስተኛ ድሉን አስመዘገበ
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 13/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ 20ኛ ሳምንት አዲስ አበባ ከተማ አርባምንጭ ከተማን 2 ለ 0 አሸንፏል።
በአበበ ቢቂላ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ አለሚ በዬቻ እና አስራት ዓለሙ ግቦቹን ከመረብ ላይ አሳርፈዋል።
ግብ ያስቆጠረችው አለሚ በዬቻ የጨዋታው ኮከብ ሆና ተመርጣለች።
አለሜ ሁለቱ ቡድኖች በመጀመሪያ ዙር ባደረጉት ጨዋታም ግብ ማስቆጠሯ የሚታወስ ነው።
በሊጉ ሶስተኛ ድሉን ያስመዘገበው አዲስ አበባ ከተማ በ11 ነጥብ ደረጃውን ከ14ኛ ወደ 13ኛ ከፍ ቢያደርግም ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል። ከአምስት ተከታታይ ሽንፈቶች በኋላ ወደ አሸናፊነት ተመልሷል።
በውድድር ዓመቱ 14ኛ ሽንፈቱን ያስተናገደው አርባምንጭ ከተማ በ10 ነጥብ ከነበረበት 13ኛ ወደ 14ኛ ዝቅ በማለት የመጨረሻውን ደረጃ ይዟል።
ቡድኑ የዛሬውን ጨምሮ ባለፉት 13 የሊግ ጨዋታዎች አላሸነፈም።
በአንጻሩ በውድድር ዓመቱ 13ኛ ሽንፈቱን ያስተናገደው ልደታ ክፍለ ከተማ በ15 ነጥብ 10ኛ ደረጃን ይዟል።
በሌላኛው መርሐ ግብር ባህር ዳር ከተማ ይርጋጨፌ ቡናን 1 ለ 0 አሸንፏል።
በአበበ ቢቂላ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ዓይናለም መኮንን በ30ኛው ደቂቃ የማሸነፊያውን ጎል አስቆጥራለች።
የባህር ዳር ከተማዋ ግብ ጠባቂ ማርታ በቀለ የጨዋታው ኮከብ ሆና ተመርጣለች።
በሊጉ አምስተኛ ድሉን ያስመዘገበው ባህር ዳር ከተማ በ16 ነጥብ ደረጃውን ከ13ኛ ወደ 10ኛ ከፍ አድርጓል። ተከታታይ ድሉንም አስመዝግቧል።
በሊጉ 13ኛ ሽንፈቱን ያስተናገደው ይርጋጨፌ ቡና በ11 ነጥብ 12ኛ ደረጃን ይዟል።
ቡድኑ ባለፉት 12 የሊግ ጨዋታዎች ከድል ርቋል።
ጨዋታዎቹን ተከትሎ 20ኛ ሳምንት ተጠናቋል።
የ21ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ከመጋቢት 15 ቀን 2018 ዓ.ም አንስቶ እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።