ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአማራ ክልል የተለያዩ የልማት ሥራዎችን ተዘዋውረው ይመለከታሉ - ኢዜአ አማርኛ
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአማራ ክልል የተለያዩ የልማት ሥራዎችን ተዘዋውረው ይመለከታሉ
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 13/2018 (ኢዜአ)፦ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በአማራ ክልል የልማት ሥራዎችን ለመመልከት ባህርዳር ገብተዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባህርዳር ደጃዝማች በላይ ዘለቀ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድርና ካቢኔያቸው፣ የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር አመራሮች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እንዲሁም የባህርዳር ከተማ ነዋሪዎች ደማቅ አቀባበል አድርገውላቸዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው የተፈጥሮ ገጸ በረከት፣ የሰላምና የውበት ተምሳሌት በሆነችው፣ ታሪክን ከለመለመ ተፈጥሮ ጋር አዛምዶ በያዘው ጣና ሐይቅና በግርማዊው ዓባይ ወንዝ በታጀበችው ውቧ ባሕር ዳር ከተማ ገብተናል ብለዋል።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድርና ካቢኔያቸው፣ የባህርዳር ከተማ አመራሮች ላደረጉላቸው ደማቅ አቀባበልም አመስግነዋል።
በምርቃታቸውና በጸሎታቸው ላልተለዩን የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እንዲሁም እንግዳን በፈገግታና በፍቅር መቀበል ለጋስ ማንነቱ ለሆነው የባሕር ዳር ከተማ ሕዝብ ከልብ የመነጨ ምስጋናዬ ይድረሳችሁ ሲሉም በመልዕክታቸው ጠቅሰዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በባህርዳር ቆይታቸው የተለያዩ የልማት ሥራዎችን ተዘዋውረው ይመለከታሉ።