ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ 20ኛ ሳምንት ዛሬ ይጠናቀቃል 

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 13/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ የ20ኛ ሳምንት የመጨረሻ ቀን ውሎ ሁለት ጨዋታዎች ይደረጋሉ። 

ከቀኑ 7 ሰዓት ላይ አርባምንጭ ከተማ ከአዲስ አበባ ከተማ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ይጫወታሉ። 

አርባምንጭ ከተማ በሊጉ ካደረጋቸው 19 ጨዋታዎች መካከል ሁለቱን ሲያሸንፍ 13 ጊዜ ተሸንፏል። በቀሪ አራት ጨዋታዎች አቻ ወጥቷል።

10 ግቦችን በጨዋታዎቹ ላይ ሲያስቆጥር 35 ጎሎችን አስተናግዷል። አርባምንጭ በ10 ነጥብ 13ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል። 

ተጋጣሚው አዲስ አበባ ከተማ በበኩሉ በውድድር ዓመቱ 19 ጨዋታዎችን አድርጎ ሁለት ጊዜ ድል ሲቀናው 15 ጊዜ ሽንፈት አስተናግዷል። በቀሪ ሁለት ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርቷል። 10 ግቦችን ከመረብ ጋር ሲያገናኝ 41 ጎሎች ተቆጥረውበታል። 


 

አዲስ አበባ ከተማ በስምንት ነጥብ የመጨረሻውን 14ኛ ደረጃን ይዟል።  አርባምንጭ ከተማ ባለፉት 12 የሊግ ጨዋታዎች አላሸነፈም። 

አዲስ አበባ ከተማ ባለፉት አምስት ተከታታይ የሊግ ጨዋታዎች ሽንፈት አስተናግዷል። በሊጉም በርካታ ሽንፈት ያስተናገደ እና በርካታ ግቦች የተቆጠሩበት ቡድንም ነው።

በወራጅ ቀጠና የሚገኙት ሁለቱ ቡድኖች ማሸነፍ ላለመውረድ በሚያደርጉት ፉክክር ወሳኝ ሶስት ነጥብ ያስገኝላቸዋል። 

በሌላኛው መርሐ ግብር ባህር ዳር ከተማ ከይርጋጨፌ ቡና ከቀኑ 9 ሰዓት በአበበ ቢቂላ  ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

ባህር ዳር ከተማ በሊጉ ባካሄዳቸው 19 ጨዋታዎች አራት ጊዜ ሲያሸንፍ በ14ቱ ተሸንፏል። በቀሪ አንድ ጨዋታ አቻ ተለያይቷል። ዘጠኝ ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ 24 ጎሎች ተቆጥረውበታል። ቡድኑ በ13 ነጥብ 11ኛ ደረጃን ይዟል። 

አዲስ አዳጊው ይርጋጨፌ ቡና በበኩሉ ከ19 የሊጉ ጨዋታዎች መካከል ሁለቱን ሲያሸንፍ 12 ጊዜ ሽንፈት አስተናግዷል። በአምስት ጨዋታዎች ደግሞ ነጠብ ተጋርቷል። በጨዋታዎቹ ላይ ዘጠኝ ግቦች ሲያስቆጥር 30 ግቦችን አስተናግዷል።

ይርጋጨፌ ቡና በ11 ነጥብ 12ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።  ባህር ዳር ከተማ ተከታታይ ድሉን ለማስመዝገብ ይጫወታል።

ባለፉት 11 የሊግ ጨዋታዎች ከድል የራቀው ይርጋጨፌ ቡና ማሸነፍ ወደ ድል መንገድ ይመልሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም