የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለሀገራት ምሳሌ የሚሆን ነው - አምባሳደር ዮሶን አርካዲዮ ሜኔስ ኮፔቴ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለሀገራት ምሳሌ የሚሆን ነው - አምባሳደር ዮሶን አርካዲዮ ሜኔስ ኮፔቴ
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 12/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለሌሎች ሀገራት ትልቅ መነሳሳትን የሚፈጥርና ምሳሌ የሚሆን ፕሮጀክት ነው ሲሉ በኢትዮጵያ የኮሎምቢያ አምባሳደር ዮሶን አርካዲዮ ሜኔስ ኮፔቴ ገለጹ።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የተጀመረው አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር እስካሁን ከ48 ቢሊዮን በላይ ችግኞች ተተክለዋል።
ይህም የአካባቢ ጥበቃን ከማጠናከር ባለፈ፣ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና ብዝሃ ህይወትን ለመጠበቅ ትልቅ ሚና እየተጫወተ ነው።
ይህ መርሃ ግብር በአፍሪካ ቀዳሚ የሆነ ግዙፍ የደን ልማትና የተፈጥሮ ጥበቃ ዘመቻ ሲሆን የካርቦን ልቀትን በመቀነስ ረገድም በምሳሌነት ተጠቃሽ ነው።
ሀገሪቱ የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋም የተፈጥሮ ሥርዓት እንድትገነባ እያገዘም ይገኛል።
በኢትዮጵያ የኮሎምቢያ አምባሳደር ዮሶን አርካዲዮ ሜኔስ ኮፔቴ ለኢዜአ በሰጡት ቃለ ምልልስ፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የሚመራው የአረንጓዴ አሻራ ፖሊሲ እጅግ የሚደነቅ ጥረት ነው ብለዋል።
አረንጓዴ አሻራ ለሌሎች ሀገራትና መሪዎች አርአያ የሚሆን ተሞክሮ እንደሚሆን ጠቁመው ይህ ተግባር ሁላችንም በጋራ እንድንሰራ ያበረታታናል ነው ያሉት።
የሀገራት መሪዎች በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት እየመጡ ያሉ ተግዳሮቶችን ለዜጎች በግልጽ ማሳወቅ እንዳለባቸውና ይህም ዜጎች ለመፍትሄው እንዲሰሩ ያደርጋል ሲሉ ገልጸዋል።
በተጨማሪም ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. በ2027 የሚካሄደውን 32ኛውን የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (ኮፕ 32) እንድታስተናግድ መመረጧን አምባሳደሩ አድንቀዋል።
ኮሎምቢያ እ.ኤ.አ. በ2024 የኮፕ 16 ጉባኤን ማስተናገዷን አውስተው ኢትዮጵያ ኮፕ 32ን በምታዘጋጅበት ወቅት ሀገራቸው ያካበተችውን ልምድ ለማካፈል ዝግጁ መሆኗን ገልጸዋል።
አምባሳደሩ አክለውም የኮሎምቢያን ተሞክሮና የኢትዮጵያን የወደፊት ራዕይ በማጣመር፣ ተግዳሮቶችን በጋራ ለመፍታት ይሰራሉ ብለዋል።