የቀብሪደሃር ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያን የኢነርጂ አቅም በዘላቂነት ለማልማት የሰው ኃይል ማፍራት ላይ ትኩረት ሰጥቷል - ኢዜአ አማርኛ
የቀብሪደሃር ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያን የኢነርጂ አቅም በዘላቂነት ለማልማት የሰው ኃይል ማፍራት ላይ ትኩረት ሰጥቷል
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 12/2018 (ኢዜአ)፡- የቀብሪደሃር ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያን የኢነርጂ አቅም በዘላቂነት ለማልማት የሚያስችል የሰው ኃይል ማፍራት ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ ራቢ (ኢ/ር) ገለጹ።
የቀብሪደሃር ዩኒቨርሲቲ እና ጂ.ሲ.ኤል ኢነርጂ ኢንቨስትመንትስ የኢትዮጵያ ቅርንጫፍ ጋር በጋራ ለመስራት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል።
ስምምነቱ በኢትዮጵያ በኢነርጂ ዘርፍ የክህሎት ልማትን፣ ኢኖቬሽን እና ዘላቂ የኢነርጂ ልማትን ለማሳደግ ያለመ እንደሆነ ተመላክቷል።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ ስምምነቱ ለዩኒቨርሲቲው ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያ የኢነርጂ ዘርፍ ትልቅ ፋይዳ አለው።
በተጨማሪም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የንድፈ ሐሳብ ትምህርትን ከኢንዱስትሪው የተግባር ልምድ ጋር በማቀናጀት ለሀገር ግንባታ የሚሆኑ ብቁ ባለሙያዎችን ለማፍራት ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያል ብለዋል።
ዩኒቨርሲቲው በዘርፉ የሚያካሂዳቸው ጥናትና ምርምሮች ለጂ.ሲ.ኤል ኢነርጂ ፕሮጀክቶች ግብዓት ከመሆናቸው ባሻገር ከኩባንያው የሚገኘው ዘመናዊ የቴክኖሎጂ ዕውቀት ለተማሪዎችና ለሀገር የኢነርጂ ዘርፍ ትልቅ አቅም ይፈጥራልም ነው ያሉት።
ዩኒቨርሲቲው የኢትዮጵያን የኢነርጂ አቅም በዘላቂነት ለማልማት የሚያስችል የሰው ኃይል ማፍራት ላይ ትኩረት መስጠቱን እንደሚያጠናክርም ተናግረዋል።
የጂ.ሲ.ኤል ኢነርጂ ኢንቨስትመንትስ የኢትዮጵያ ቅርንጫፍ ፕሬዚዳንት ሱን ዦንግ እንዳሉት፤ ስምምነቱ በቻይና እና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን የኢንዱስትሪ እና የትምህርት ትስስር ለማሳደግ የሚያስችል ነው።
በአካዳሚክ እና በኢንዱስትሪ መካከል የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ ትብብር ለመፍጠር ትልቅ ምዕራፍ እንደሆነም አስረድተዋል።
ጂ.ሲ.ኤል በኢነርጂ፣ ኢንጂነሪንግ፣ በቴክኒክ፣ በትምህርት፣ በምርምርና ፈጠራ ዘርፍ ጠንካራ አቅም እንዲሁም ውጤታማ የሰው ኃይል ለማፍራት እንደ ቁልፍ ማዕከል እንደሚያገለግል አስገንዝበዋል።