የዜጎችን የሥርዓተ ምኅዳር አገልግሎት ክፍያ ለሚያሻሽሉ መመሪያዎች ተፈፃሚነት ጥብቅ ቁጥጥር ይደረጋል - ኢዜአ አማርኛ
የዜጎችን የሥርዓተ ምኅዳር አገልግሎት ክፍያ ለሚያሻሽሉ መመሪያዎች ተፈፃሚነት ጥብቅ ቁጥጥር ይደረጋል
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 12/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ የዜጎችን የሥርዓተ ምኅዳር አገልግሎት ክፍያ የሚያሻሽሉ መመሪያዎችን በማውጣት ለተግባራዊነታቸው ጥብቅ ቁጥጥር እንደሚደረግ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውሃ፣ መስኖ፣ ቆላማ አካባቢዎችና የአካባቢ ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አወቀ አምዛዬ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ከፋርም አፍሪካና ኤስ.ኦ.ኤስ ሳህል ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር በሥርዓተ ምህዳር አገልግሎት ክፍያ ትግበራ ላይ ትኩረት ያደረገ የውይይት መድረክ አካሂዷል፡፡
የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን የባለድርሻ ተቋማትን ትብብር በማጠናከር በደንብ ቁጥር 545/2016 በተሰጠው ኃላፊነት መሰረት የሥርዓተ ምኅዳር አገልግሎት ክፍያ ሥርዓትን ይከታተላል፤ ይቆጣጠራል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ አወቀ አምዛዬ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ ተፈጥሮ የቸራትን ዕምቅ የብዝኅ ህይወት ሃብት በሚገባት ልክ ጥቅም ላይ እያዋለች እንዳልሆነ ገልጸዋል።
ለዚህም የውሃና የየብስ የሥነ-ምኅዳር ጸጋዎች ለሀገር የኢኮኖሚ ጥቅም ለማዋል የሚስችል "የሥርዓተ ምኅዳር አገልግሎት ክፍያ አዋጅ ቁጥር 140/2018" ተግባራዊ መደረጉን አስታውቀዋል።
ምክር ቤቱም ከመንግስተና የዘርፉ ተዋናዮች ጋር የግብዓት ማሰባሰቢያ መድረኮችን በማዘጋጀት ግብዓት ታክሎበት አዋጁን በማፅደቅ ሥራ ላይ እንዲውል መደረጉን ተናግረዋል።
በዚህም የዜጎችን የሥርዓተ ምኅዳር አገልግሎት ክፍያ ለማሻሻል የሚረዱ የማስፈጸሚያ ደንቦችና መመሪያዎች መውጣታቸውንና ተፈፃሚነ መሆናቸውን ጥብቅ ክትትል እንደሚደረግ አንስተዋል።
የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ንጉሱ ለማ፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ የተቀናጀ የሥነ-ምህዳር አገልግሎት የክፍያና የሕግ ማዕቀፍ እንዳለነበረ ገልጸዋል፡፡
በዚህም የኢትዮጵያ ሥርዓተ ምኅዳር ዘላቂነት ለማስጠበቅ የመንግስትና የባለድርሻ ተቋማትን ፍላጎት ታሳቢ ያደረገ የሥርዓተ ምኅዳር አገልግሎት ክፍያ አዋጅ ቁጥር 140/2018 መፅደቁን ተናግረዋል።
የአገልግሎት ክፍያ የአሰራር ሥርዓቱም የኢኮኖሚ ዕድልን በመፍጠርና ለአገልግሎቱ አቅራቢዎች ዘላቂ ዋስትናን ይፈጥራል ብለዋል፡፡
አዋጁን መነሻ በማድረግ የዘርፉን ተዋናዮች ተሳትፎ ማሳደግ የሚያስችል የማስተግበሪያ መመሪያ መዘጋጀቱን አስረድተዋል።
የፋርም አፍሪካ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ሸዊት አማኑኤል፤ ኢትዮጵያ ደኖችን በመንከባከብ የበካይ ጋዝ ልቀትን በመቀነስ ለዓለም የከባቢ አየር ሥነ ምህዳር ገንቢ ሚና እየተወጣች መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያዊያን ደንን በመንከባከብ በአየር ንብረት ለውጥ ቅነሳ በሚበረክቱት አስተዋፅኦ ልክ ሳይንሳዊ ጥናትና ኦዲት ተካሂዶ ገቢ ማመንጨት መጀመሩን አንስተዋል።
የሥርዓተ ምኅዳር አገልግሎት ክፍያ አዋጅ በባሌ አካባቢ የተጀመረውን በሌሎች አካባቢዎች ለማስፋት በር የሚከፍት መልካመ ዕድል መሆኑንም ተናግረዋል፡፡