ቀጥታ፡

የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የደን ሽፋንን በማሳደግ ዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ እያበረከተ ይገኛል

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 12/2018 (ኢዜአ)፦ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የኢትዮጵያን የደን ሽፋን በማሳደግ ዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ እያበረከተ እንደሚገኝ የግብርና ሚኒስትር አዲሱ አረጋ ገለጹ።

የፌዴራልና የክልል መንግስታት የግብርና ዘርፍ የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት ''የመደመር መንግሥት የተፈጥሮ ሃብት ዕይታ'' በሚል መሪ ሃሳብ የዓለም አቀፍ የደን ቀን የምክክር መድረክ ተካሂዷል፡፡


 

በመድረኩ የግብርና ሚኒስትር አቶ አዲስ አረጋ፤ የመደመር መንግሥት ለአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የሰጠው ትኩረት የተፈጥሮ ሃብቶችን በማስጠበቅ ዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ማበርከት ያስቻለ ውጤት መገኘቱን ገልጸዋል።

በዚህም ባለፉት ስምንት የለውጥ ዓመታት ከ48 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን በመትከል የኢትዮጵያን የደን ሽፋን ወደ 23 ነጥብ 6 በመቶ ማሳደግ እንደተቻለ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያን የተራቆተ የመሬት ገፅታ በደን በመሸፈን የአፈር መሸርሸርና የሥነ-ምኅዳር ደኅንነትን መጠበቅ ያስቻለ ውጤት እየተገኘ መሆኑንም አንስተዋል።

ቡናን ጨምሮ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የሚተከሉ ችግኞች የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ ዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ እያበረከቱ እንደሚገኝ አብራርተዋል።

በቀጣይም የማህበረሰቡን የደን ጥበቃ ግንዛቤ በማሳደግና የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በማስቀጠል በትኩረት እንደሚሰራ አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርና የደን ልማት ስኬትም የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን በመቀነስ የግብርና ምርታማነትን እያሳደገ እንደሚገኝ አብራርተዋል።

ለአብነትም ከሰባት ዓመታት በፊት ወደ ውጭ ይላክ የነበረን 230 ሺህ ቶን የቡና ምርት አሁን ላይ ወደ 475 ሺህ ቶን በማሳደግ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ማግኘት እንደተቻለ አንስተዋል።


 

የኢትዮጵያ ደን ልማት ዋና ዳይሬክተር ከበደ ይማም በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ የደን ሃብት ልማት መርሃ ግብር ዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ እያስገኘ ነው ብለዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት በ2011 ዓ.ም የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ስኬታማነትም ከክልልና ባለድርሻ ተቋማት ጋር በቅንጅት መሰራቱን አንስተዋል።


 

የአረጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የቴክኒክ ኮሚቴ አስተባባሪ አደፍርስ ወርቁ (ዶ/ር)፤ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ያስገኘውን ስኬትና ቀጣይ ሥራ የሚዳስስ የመነሻ ጽሁፍ አቅርበዋል።

ይህም የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የዓባይ ተፋሰስ ወረዳዎችን የተራቆተ የመሬት ገፅታ በደን በመሸፈን የከርሰና የገፀ ምድር ሃብቶች ላይ ዘርፍ ብዙ ጠቀሜታ እያስገኘ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም