ቀጥታ፡

ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ዴሞክራሲያዊ እና አሳታፊ እንዲሆን የድርሻዬን እየተወጣሁ ነው -ኦቢኤን

አዳማ፤ መጋቢት 12/2018 (ኢዜአ)፦ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ዴሞክራሲያዊ እና አሳታፊ እንዲሆን የድርሻውን እየተወጣ መሆኑን የኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኦቢኤን) አስታወቀ።

በምርጫ ወቅት መገናኛ ብዙሃን ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታና ለምርጫው ስኬታማነት የማይተካ ሚና ያላቸው ሲሆን በተለይም መረጃን ተደራሽ ማድረግና ግንዛቤ መፍጠር፣ የፖለቲካ አማራጮችን ማስተዋወቅና የምርጫ ክርክሮችን ያዘጋጃሉ።

ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ዴሞክራሲያዊ፣ ሰላማዊ፣ አሳታፊ እና አካታች እንዲሆን መገናኛ ብዙሃን እንደ ባለድርሻ አካል ሚናቸውን እየተወጡ ይገኛሉ።

በዚሁ ጉዳይ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው የኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኦቢኤን) ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አንዋር ጀማል ተቋሙ ስርጭት በሚያከናውንባቸው ሁሉም ቋንቋዎች ምርጫውን በተመለከተ ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

ሕዝቡ በቂ ግንዛቤ ጨብጦ በምርጫው የነቃ ተሳትፎ እንዲኖረው ከማድረግ አንጻር ሁሉንም የምርጫ ባለድርሻ አካላት ባሳተፈ መልኩ ጥረት እያደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።

በተለይም የፖለቲካ ፓርቲዎች የየራሳቸውን ፖሊሲ፣ ስትራቴጂና አማራጭ ሃሳቦች ለሕዝቡ ማስተዋወቅ እንዲችሉ እድል ተሰጥቷቸዋል ብለዋል።

ከዚህም ባለፈ ተከታታይ የምርጫ ክርክር መድረኮችን በማዘጋጀት የምርጫ ማኑፌስቷቸውን እንዲያስተዋውቁ እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።

ተፎካካሪ ፓርቲዎች ተቋሙ ለስርጭት በሚጠቀምባቸው ቋንቋዎች አማራጭ ሃሳባቸውን ለሕዝብ ተደራሽ ማድረጋቸው የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋትና የምርጫ አውዱ እንዲጠናከር የጎላ ሚና እንዳለውም አስረድተዋል።

ተቋሙ የምርጫ ዴስክ በማደራጀት በጠቅላላ ምርጫው ዙሪያ ሰፋ ያሉ ስራዎችን እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው ለጋዜጠኞች በምርጫ ሥነ-ምግባር፣ ደንቦችና ሕጎች ላይ በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸው የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎች እየተሰጡ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም በቅድመ ምርጫ፣ በምርጫ ወቅትና በድህረ ምርጫ ወቅት የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ሊከተሏቸው በሚገቡ የሙያ ሥነ-ምግባርና የዘገባ አዘጋገብ ዘዴዎች ላይ ተከታታይ ሥልጠናዎች እየተሰጡ መሆኑንም ገልጸዋል።

ተቋሙ ከቴሌቪዥን ጣቢያው ባሻገር በኮርፖሬሽኑ ሥር ባሉ የኤፍ.ኤም ሬዲዮዎች በየዞኑ ጠቅላላ ምርጫውን የተመለከቱ ስራዎችን በስፋት እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም