ቀጥታ፡

በመሬት ናዳ የተፈናቀሉ ወገኖችን ለማቋቋም የባለድርሻ አካላት ሚና እንዲጠናከር ጥሪ ቀረበ

አርባምንጭ፤ መጋቢት 12/2018 (ኢዜአ)፡- በጋሞ ዞን በመሬት ናዳ አደጋ የተፈናቀሉ ወገኖችን በዘላቂነት ለማቋቋም በሚደረገው ጥረት የባለድርሻ አካላት ሚና እንዲጠናከር የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ጥሪ አቀረበ።


 

ኮሚሽንኑ በጋሞ ዞን በመሬት ናዳ አደጋ የተፈናቀሉ ወገኖችን መልሶ ለማቋቋም በሚያስችሉ ሳይንሳዊ ጥናቶች ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር ተወያይቷል።

የኮሚሽንኑ ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት፤ በመሬት ናዳ አደጋ የተፈናቀሉትንና በአደጋ ስጋት ላይ የሚገኙ ሰዎችን መልሶ ለማቋቋም ተቋማቸው ሚናውን እንደሚወጣ ገልጸዋል።

የበልግ ዝናቡ እንደሚቀጥል ጠቁመው፤ ተጨማሪ ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳት እንዳይደርስ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓት በትኩረት እንዲሠራ አሳስበዋል።


 

የተለያዩ አጋሮች የዕለት ደራሽ ድጋፍ ከማድረግ ጎን ለጎን ተፈናቃዮችን በዘላቂነት ለማቋቋም በሚደረጉ ጥረቶች እየተወጡ ያለውን አስተዋፅዖ እንዲያጠናክሩም ጠይቀዋል።

ተፈናቃዮች በሚሰፍሩባቸው አካባቢዎች ትምህርት፣ ጤና፣ የንጹህ መጠጥ ውኃ አገልግሎትን ጨምሮ የማኅበራዊና የመሠረተ-ልማት ሥራዎችን በማከናወን ከመንግሥት ጎን መቆም እንዳለባቸው አመልክተዋል።


 

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አደጋ ስጋት አመራርና የምግብ ዋስትና ኮሚሽን ኮሚሽነር ወገኔ ብዙነህ በበኩላቸው፤ ተፈናቃዮችን በዘላቂነት ለማቋቋም በዞኑ የተለያዩ ወረዳዎች ቦታዎች መዘጋጀታቸውን አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም