ቀጥታ፡

የሐይማኖት አባቶች ችግሮችን በምክክር በመፍታት ለዘላቂ ሰላም መሥራት እንደሚገባ አስገነዘቡ

ገንዳ ውኃ፣ ጎንደር፤ መጋቢት12/2018 (ኢዜአ)፡- የአብሮነት እሴቶችን በማጎልበት ችግሮችን በምክክር በመፍታት ለዘላቂ ሰላምና ልማት በጋራ መሥራት እንደሚገባ የሐይማኖት አባቶች አስገነዘቡ።

የገንዳ ውኃ ከተማ እስልምና ምክር ቤት ሰብሳቢ ሼኽ አሕመድ ኑርዬ እና የከተማዋ ነዋሪ ሼኽ ሙሀመድ ይማም፤ ለኢትዮጵያ አሁን ላይ ከምንም በላይ ሰላምና ልማት ያስፈልጋታል ብለዋል።
 
የምንም ነገር መሠረቱ ሰላም መሆኑን አስገንዝበው፤ የሰላም ቁልፍ ያለው ደግሞ በእያንዳንዳችን ዕጅ ላይ በመሆኑ ለሰላምና ልማት መሥራት የጋራ ኃላፊነታቸን ነው ሲሉ ለኢዜአ ተናግረዋል። 
 
የአብሮነት ዕሴቶችን በማጎልበት ችግሮችን በምክክር በመፍታት ለዘላቂ ሰላምና ልማት በመሥራት የጋራ ጥረታችን ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባልም ነው ያሉት።

በተለያዩ ምክንያቶች ለቅራኔ የዳረጉ ሀገራዊ ችግሮችን በመቀራረብ በውይይት በመፍታት ዘላቂ ሰላምና ልማት ማምጣት እንዲሁም ሀገራዊ አንድነትን ማጥበቅ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የጎንደር ከተማ ነዋሪ ሀጂ ኡመር ዳውድ፣ ሼህ ከማል አደም እና ሰይድ ጀማል በበኩላቸው፤ የሐይማኖት አባቶች ከልዩነት ይልቅ የሚያቀራርቡ፣ ሰላምን የሚያጸኑ እና አንድነትን የሚያጠብቁ ተግባራት ላይ አተኩረን መሥራት ይጠበቅብናል ብለዋል።

የቆዩ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ሁሉንም ያሳተፈ የምክክር ሂደት መጀመሩ ለዘላቂ ሰላም ጥሩ መሰረት የሚያኖር ስለመሆኑም አስረድተዋል።

በምክክር ችግሮችን ለመፍታት የሁላችንም ዝግጁነት ያስፈልጋል ሲሉም ገልጸዋል።

ወጣቶች ስለ ሀገር ፍቅር፣ ሰላምና አብሮነት ዝግጁ ሆነው መሥራት እንዳለባቸውና የሐይማኖት መሪዎችም በዚሁ ልክ ማስተማር ይገባናል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም