የሐይማኖት አባቶች ለሰላም ዕሴት መዳበር የሚያደርጉትን አስተዋጽዖ በይበልጥ ሊያጠናክሩ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የሐይማኖት አባቶች ለሰላም ዕሴት መዳበር የሚያደርጉትን አስተዋጽዖ በይበልጥ ሊያጠናክሩ ይገባል
ባሕር ዳር፤ መጋቢት 12/2018 (ኢዜአ)፦ በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የሐይማኖት አባቶች የሰላም፣ አብሮነትና የመቻቻል ዕሴትን ለማጎልበት የሚያደርጉትን አስተዋጽዖ አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ተገለጸ።
የከተማ አሥተዳደሩ “በመደመር ዕይታ የሐይማኖት ተቋማት መሪዎች ሚና” በሚል መሪ ሐሳብ በባሕር ዳር ከተማ ከሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ቤተ ክርስቲያን አባቶች ጋር የውይይት መድረክ አካሂዷል።
የአሥተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው በዚሁ ወቅት፤ ቤተ ክርስቲያኗ በሀገር ግንባታ እንዲሁም ሰላም መስፈን ረገድ ድርሻዋን እየተወጣች ነው ብለዋል።
የከተማዋን ሰላምና ፈጣን ልማት ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የሐይማኖት መሪዎችና የምእመኑ ድጋፍ በይበልጥ ሊጠናከር እንደሚገባም አመላክተዋል።
በቀጣይም በከተማ አሥተዳደሩ የሚገኙ የሐይማኖት አባቶች ለሰላምና አብሮነት የሚያደርጉትን አስተዋጽዖ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።
የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መላከ ሰላም ኤፍሬም ሙሉዓለም በበኩላቸው፤ ሰላም ለማንኛውም ሐይማኖታዊና ማኅበራዊ እንቅስቃሴ መሠረታዊ ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል።
ቤተ ክርስቲያኗ በመደበኛ የጸሎትና የትምህርት ሥርዓቶቿ ሁሉ ለሰላም መስፈን ልዩ ትኩረት ሰጥታ እየሠራች መሆኑን አስረድተዋል።
በቀጣይም ለሰላም የምታደርገውን ጥረት እንደምታጠናክር ጠቁመው፤ አሥተዳደሩ ከተማዋን ለማሳደግ እያደረገ ያለው ጥረት የሚደነቅና የሚደገፍ መሆኑን አረጋግጠዋል።