ለኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ መጎልበት በምርጫ ሂደት የዜጎች የነቃ ተሳትፎ ወሳኝ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ለኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ መጎልበት በምርጫ ሂደት የዜጎች የነቃ ተሳትፎ ወሳኝ ነው
ዲላ፤ መጋቢት 12/2018 (ኢዜአ):- ለኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ መጎልበት በምርጫ ሂደት የዜጎች የነቃ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑ ተገለጸ።
"በኢትዮጵያ ምርጫ የማካሔድ ፋይዳዎች ለሀገር ግንባታ፣ ለሰላም፣ ለልማት እና ብልፅግና ያለው አንደምታ" በሚል መሪ ሃሳብ በዲላ ዩኒቨርሲቲ የውይይት መድረክ ተካሂዷል።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሚንቀሳቀሱ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና ተወካዮች፣ በርካታ ምሁራን እና የተለያዩ ባለደርሻ አካላት በመድረኩ ተገኝተዋል።
በመድረኩ የውይይት መነሻ ጽሁፍ ያቀረቡት የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የማህበራዊና ስነ-ሰብ ኮሌጅ ዲን፣ መምህርና ተመራማሪ ፕሮፌሰር ዘለቀ አርፍጮ፤ የምርጫ ሂደት ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ መሰረታዊ ጉዳይ መሆኑን አንስተዋል።
የምርጫ ሂደት የዜጎችን የፖለቲካ ተሳትፎና የመወሰን መብት የሚያጎናጽፍ እና ፓርቲዎችም ለሀገርና ህዝብ የሚጠቅሙ ፖሊሲና ስትራቴጂዎች የሚያመነጩበት ስለመሆኑ አስረድተዋል።
በመሆኑም ለኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ መጎልበት በምርጫ ሂደት የዜጎች የነቃ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።
በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ እስካሁን የፖለቲካ ፓርቲዎች ፉክክርና የህዝቡ ተሳትፎ በጥሩ መልኩ እየተካሄደ መሆኑን አንስተው ቀጣይነት ሊኖረው እንደሚገባ ገልጸዋል።
የዲላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ኤልያስ ዓለሙ (ዶ/ር)፤ በበኩላቸው በሁሉም ረገድ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ በማካሄድ የኢትዮጵያን ሀገረ መንግስት ግንባታ ማጽናት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በመሆኑም በዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሀሳባቸውን እንዲያንሸራሽሩ መድረክ በመፍጠር ዜጎች የጠራ ግንዛቤ ይዘው መምረጥ እንዲችሉ ሚዲያዎች ሃላፊነታቸውን መወጣት አለባቸው ብለዋል።
ለኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ መጎልበት በዘንደሮው ጠቅላላ ምርጫ የፖለቲካ ፓርቲዎች አማራጭ ሃሳቦች እንዲሁም የዜጎች የነቃ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑንም አስገንዝበዋል።