ቀጥታ፡

በመጪው ክረምት የሚተከሉ የተሻሻሉ የቡና ችግኞች ዝግጅት እየተከናወነ ነው

ጊምቢ፤ መጋቢት 12/2018 (ኢዜአ)፦ በምዕራብ ወለጋ ዞን በመጪው ክረምት የሚተከሉ የተሻሻሉ የቡና ችግኞች ዝግጅት በስፋት እየተካሄደ መሆኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ ኃላፊ ፈይሳ ሀምቢሳ አስታወቁ።


 

የቡና ችግኙ በሦስት ዓመት ውስጥ ምርት መስጠት የሚችል መሆኑን ጠቁመው፤ በሔክታር እስከ 12 ኩንታል ምርት እንደሚያስገኝ ለኢዜአ አረጋግጠዋል።

በአሁኑ ወቅትም ከ370 ሚሊየን በላይ ችግኞች መዘጋጀታቸውን እና ለተከላ የሚውል የጉድጓድ ቁፋሮን ጨምሮ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ዝግጅት እየተከናወነ ነው ብለዋል።

የተሻሻሉት ችግኞች የቡና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ ባለፈ፤ ከቡና የሚገኘውን የውጭ ምንዛሬ ለማሳደግ ጉልኅ አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸው አስረድተዋል።   

በሌላ በኩል ከ66 ሺህ ሔክታር በሚልቅ መሬት ላይ የሚገኝና ምርት የማይሰጥ ያረጀ ቡናን የመንቀል ሥራ እየተከናወነ መሆኑን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም