ቀጥታ፡

በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ህዝቡ የተለያዩ ሀሳቦችን እንዲያገኝ ምቹ ሁኔታ እየፈጠርን ነው - የሚዲያ ተቋማት

ሐዋሳ፤ መጋቢት 12/2018 (ኢዜአ) :- በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የፖለቲካ ፓርቲዎች አማራጭ ሀሳባቸውን ለህዝብ እንዲያቀርቡ መረጃን ተደራሽ በማድረግ ምቹ ሁኔታን እየፈጠሩ መሆናቸውን የተለያዩ የሚዲያ ተቋማት ገለጹ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ጠቅላላ ምርጫ ለማካሔድ ቀነ ቀጠሮ መያዙ የሚታወቅ ሲሆን ተሳታፊ ፓርቲዎችም የተለያዩ የቅድመ ዝግጅት ተግባራትን እያከናወኑ ይገኛሉ።

በዚህም ተፎካካሪ ፓርቲዎች ያሏቸውን አማራጮችና የፓርቲ ፕሮግራም ለመራጩ ህዝብ የማስተዋወቅና የክርክር መድረኮችን በማካሔድ ላይ የሚገኙ ሲሆን በሀገሪቱ የሚገኙ የሚዲያ ተቋማትም ይህን ሃላፊነት እየተወጡ ይገኛሉ።

ይህም መራጩ ህዝብ የፖለቲካ ፓርቲዎቹን የፖሊሲ አማራጭ ጠንቅቆ በማወቅ ትክክለኛ ውሳኔ እንዲወስን እድልን እንደሚፈጥር እሙን ነው።

ኢዜአ የደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት እና የሲዳማ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን የሥራ ሃላፊዎችን በምርጫው ዙሪያ ለህዝቡ መረጃዎችን በማድረስ ረገድ ሃላፊነታቸውን ለመወጣት እያከናወኑት ስላለው ተግባር ጠይቋል።


 

የደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ዋና ስራ አስፈጻሚ ዘላለም ገነሞ እንዳሉት ድርጅቱ ለምርጫው ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት የፖለቲካ ፓርቲዎች ይዘው የመጡትን የፖሊሲ አማራጮች እንዲያስተዋውቁ እያደረገ ይገኛል።

በደቡብ ኢትዮጵያ፣ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ በሲዳማና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልሎች የሚንቀሳቀሱና በምርጫው የሚሳተፉ ፓርቲዎች በቴሌቪዥን የሚከራከሩበትን መድረክ በማዘጋጀት አመራጮቻቸውን እንዲያስተዋውቁ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩንም ተናግረዋል።

የደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት በዋና ጣቢያውና ባሉት ቅርንጫፎች በሬዲዮ፣ በቴሌቪዥን፣ በዲጂታል ሚዲያውና በጋዜጣ በ50 ቋንቋዎች ስለምርጫው ለህዝብ መረጃ እያደረሰ እንደሚገኝ አቶ ዘላለም ገልጸዋል።

ድርጅቱ ከምርጫ ቦርድና ከኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሀን ባለስልጣን ጋር በቅንጅት እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸው በቀጣይ ለፓርቲዎቹ በሚሰጠው የአየር ሰዓት ድልድል መሰረት ለማስተናገድ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን አስታውቀዋል።


 

የሲዳማ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ምክትል ስራ አስፈጻሚና የይዘት ዘርፍ ኃላፊ አቶ አደገ አየለ ሲቢሲ በምርጫው የሚሳተፉ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሚኖራቸው መድረኮች በመገኘት መረጃዎችን ለህዝቡ እያደረሰ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ኮርፖሬሽኑ አጀንዳ በመቅረጽ ምርጫን በተመለከተ ከህብረተሰቡ ጋር ውይይቶችን በማድረግ አስተያየቶችን በመሰብሰብ እየሰራ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።

ለማህበረሰቡ በሲዳምኛና በአማርኛ ቋንቋዎች ምርጫውን የተመለከቱ መረጃዎች እንዲደርሱት በቴሌቪዥንና በዲጂታል ሚዲያው እያሰራጨ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም