የተፈጥሮ ሃብት አገልግሎት አቅራቢዎች ለሥነ-ምኅዳር ደኅንነት በይበልጥ ሊተጉ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የተፈጥሮ ሃብት አገልግሎት አቅራቢዎች ለሥነ-ምኅዳር ደኅንነት በይበልጥ ሊተጉ ይገባል
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 12/2018 (ኢዜአ)፡- የተፈጥሮ ሃብት አገልግሎት አቅራቢዎች የአካባቢ ጥበቃ ባህልን በማሳደግ ለሥነ-ምኅዳር ደኅንነት ይበልጥ ሊሠሩ እንደሚገባ የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን አሳሰበ።
ባለሥልጣኑ ከፋርም አፍሪካ እና ኤስ.ኦ.ኤስ ሳህል ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር በሥርዓተ-ምኅዳር አገልግሎት ክፍያ ትግበራ ላይ ትኩረት ያደረገ የውይይት መድረክ እያካሄደ ነው።
በዚሁ ወቅትም የባለሥልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ንጉሡ ለማ፤ ተቋማቸው የሥርዓተ-ምኅዳር አገልግሎት ክፍያ ሥርዓትን የመከታተልና የመቆጣጠር ኃላፊነት እንዳለበት ገልጸዋል።
በዚህም የኢትዮጵያን ሥርዓተ-ምኅዳር ዘላቂነት ለማስጠበቅ የመንግሥትና የባለድርሻ ተቋማትን ፍላጎት ታሳቢ ያደረገ የሥርዓተ-ምኅዳር አገልግሎት ክፍያ አዋጅ ቁጥር 140/2018 መጽደቁን አስረድተዋል።
የሥርዓተ-ምኅዳር የአገልግሎት ክፍያ የአሠራር ሥርዓቱም ለተጠቃሚዎችና አገልግሎት አቅራቢዎች ምቹ የክፍያ መፈጸሚያ ሁኔታ እንደፈጠረ አረጋግጠዋል።
ይህም የሥርዓተ-ምኅዳር አገልግሎት አቅርቦትን በማሻሻልና ዘላቂነት እንዲኖረው ከፍተኛ እገዛ ያደርጋል ብለዋል።
አዋጁም ከዚህ በፊት ክፍያ ያልተተመነላቸው የሥርዓተ-ምኅዳር አገልግሎቶች ላይ የዋጋ ተመን በማስቀመጥ የኢኮኖሚ ዕድልን እንደሚፈጥር አስረድተዋል።
ለአዋጁ ገቢራዊነት የዘርፉ ተዋንያን ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው፤ ባለሥልጣኑ ለአዋጁ ማስፈጸሚያነት የሚየገለግሉ መመሪያዎች ማዘጋጀቱን አስታውቀዋል።