የምርጫ ካርድ በመያዝ ለኢትዮጵያ የተሻለ የሚሰራውን ለመምረጥ ተዘጋጅተናል - የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
የምርጫ ካርድ በመያዝ ለኢትዮጵያ የተሻለ የሚሰራውን ለመምረጥ ተዘጋጅተናል - የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች
ሚዛን አማን፤ መጋቢት 12/2018 (ኢዜአ)፦ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በመሳተፍ ለኢትዮጵያ እድገት በንቃት መስራት የሚችለውን የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ ዝግጁ ሆነናል ሲሉ የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ተናገሩ።
ኢትዮጵያ 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ አካታች፣ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ለማከናወን የተለያዩ የቅድመ ምርጫ ሂደቶችን እየተገበረች ነው።
ምርጫው በአሳታፊነቱ ሴቶች፣ አካል ጉዳተኞችና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎችንም የሚያካትት በመሆኑ ኢዜአ ከሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ጋር ቆይታ አድርጎ ተማሪዎቹ በምርጫው ለመሳተፍ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በትምህርት ላይ ቢሆኑም ያላቸውን ጊዜ በመጠቀም ካርድ ወስደው በሀገር ጉዳይ ላይ በድምጽ የመወሰን ሕገ መንግስታዊ መብታቸውን እንደሚጠቀሙበትም አረጋግጠዋል።
የዩኒቨርሲቲው ተማሪ ጌታቸው በላቸው ለመጀመሪያ ጊዜ በምርጫ እንደሚሳተፍ ገልጾ ለዚህም የምርጫ ካርድ በመውሰድ የተሻለ ሀሳብ የያዘ ፓርቲ ለመምረጥ መዘጋጀቱን ተናግሯል።
በዚህም ካርዱን በመውሰድ የምርጫው ጊዜውን በጉጉት እየጠበቀች መሆኑን የተናገረችው ደግሞ ተማሪ ሰናይት ረዳይ ነች።
እንደ ዜጋ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ መሳተፍ ግዴታችን በመሆኑ በእያንዳንዱ የምርጫ ሂደት ሕጉ በሚፈቅደው መንገድ ተሳትፈን የዴሞክራሲ ልምምድን ማጠናከር አለብን ብላለች።
ተማሪ ታምሩ ገብረ ማርያም እና ተማሪ አቤል ሳምሶን በበኩላቸው በካርድ ድምጻችንን ለመስጠት የሚያስችል ዝግጅት ከወዲሁ እያደረግን ነው ብለዋል።
ከመምረጥ ባሻገር የምንመርጠውን ፓርቲ ፖሊሲ ለይቶ መረዳትና ለኢትዮጵያ እድገት የተሻለ የሚሰራውን በቅድመ ምርጫ ጊዜ መለየት ይጠበቅብናል የሚል ሀሳብ አጋርተዋል።
ሌሎች ተማሪዎችም በትምህርት የሚያውቁትን የምርጫ ሥነ ሥርዓት በተግባር ለማረጋገጥ የሚያስችላቸውን ካርድ ተመዝግበው መውሰድና ለምርጫው መዘጋጀት እንዳለባቸውም አመልክተዋል።