ቀጥታ፡

ነጻ የዓየር ሠዓት አጠቃቀም ለምርጫ ሂደት ዴሞክራሲያዊነት ወሳኝ ሚና አለው

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 12/2018 (ኢዜአ)፡- የነጻ የዓየር ሠዓት አጠቃቀም ለምርጫ ሂደት ዴሞክራሲያዊነት እና ፍትሐዊነት ወሳኝ ሚና እንዳለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ ተስፋዬ ንዋይ ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን እና የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች በተገኙበት፤ በፖለቲካ ፓርቲዎች ነጻ የዓየር ሠዓት ድልድልና አጠቃቀም ላይ የምክክር መድረክ እየተካሄደ ነው፡፡


 

አቶ ተስፋዬ ንዋይ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ ነጻ የዓየር ሠዓት ፖለቲካ ፓርቲዎች ፕሮግራማቸውንና ማኑፌስቷቸውን ለሕዝብ የሚያስተዋውቁበት ወሳኝ መድረክ ነው።

ይህ አሠራር የምርጫ ሂደቱ ዴሞክራሲያዊ፣ ግልጽ እና ፍትሐዊ መሆኑን ከሚያሳዩ መገለጫዎች አንዱ ነው ብለዋል።

ቦርዱ ከመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ጋር በመተባበር ነጻ የዓየር ሠዓት አጠቃቀምን የሚመራ መመሪያ አዘጋጅቶ ወደ ሥራ መግባቱንም አስታውቀዋል።


 

ፓርቲዎች በመገናኛ ብዙኃን የሚሰጣቸውን ነጻ የዓየር ሠዓት እና የጋዜጣ ዐምድ ለምርጫ ቅስቀሳ ሥራቸው በአግባቡ እንዲጠቀሙበት ጥሪ አቅርበዋል።

ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ እስካሁን ከ18 ነጥብ 5 ሚሊየን በላይ ዜጎች ለመራጭነት መመዝገባቸውንም አመላክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም