በሙያ ሥነ-ምግባር የታነፀ ጋዜጠኛ ለሀገር ግንባታ የማይተካ ሚና ይጫወታል - ኢዜአ አማርኛ
በሙያ ሥነ-ምግባር የታነፀ ጋዜጠኛ ለሀገር ግንባታ የማይተካ ሚና ይጫወታል
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 12/2018 (ኢዜአ)፡- በሙያ ሥነ-ምግባርና በልኅቀት የታነፀ ጋዜጠኛ ለሀገር ግንባታ የማይተካ ሚና እንደሚጫወት የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሐይማኖት ዘለቀ ገለጹ፡፡
በባለሥልጣኑ የልኅቀት ማዕከል የተዘጋጀ የልዩ ትኩረት ዘርፍ ጋዜጠኝነት ሥልጠና ማጠናቀቂያ መርሐ-ግብር እየተካሄደ ነው፡፡
ዋና ዳይሬክተሯ በዚሁ ወቅት፤ ሥልጠናው በኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙኃን ታሪክ ውስጥ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ እና ለዘርፉ እድገት ትልቅ አበርክቶ የሚኖረው መሆኑን ተናግረዋል።
በሙያ ልኅቀት የታነፀ ጋዜጠኛ ለሀገር እድገት ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበው፤ ሠልጣኞች በቀጣይ በዋና ዋና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ለሕዝብ በበቂ ሁኔታ እንደሚያሳውቁ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
ለ21 ቀናት በተጠናከረ መልኩ ሲሰጥ የቆየው ይህ ሥልጠና፤ ወቅቱን የጠበቀ እና ዘርፉን የሚያዘምን መሆኑንም አስታውቀዋል።
ይህ የልኅቀት ጉዞ መጀመሪያ እንጂ መዳረሻ አለመሆኑን በማስገንዘብ ባለሙያዎቹ በቀጣይ በየተቋማቸው ለውጥ እንዲያመጡ ጥሪ አቅርበዋል።
ከሕዝብና ከግል መገናኛ ብዙኃን የተውጣጡት እነዚህ 36 ባለሙያዎች በዘርፉ ልዩ ክኅሎት እንዲኖራቸው የሚያስችል ሥልጠና መውሰዳቸውንም አረጋግጠዋል።