በፕሪሚየር ሊጉ መቻል ከቦሌ ክፍለ ከተማ ጋር ይጫወታል - ኢዜአ አማርኛ
በፕሪሚየር ሊጉ መቻል ከቦሌ ክፍለ ከተማ ጋር ይጫወታል
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 12/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 20ኛ ሳምንት ዛሬ ሁለት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።
ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ መቻል ከቦሌ ክፍለ ከተማ በአበበ በቂላ ስታዲየም ይጫወታሉ።
መቻል በሊጉ እስከ አሁን ያሸነፋቸው ጨዋታዎች ብዛት 12 ናቸው። ሁለት ጊዜ ሲሸነፍ አምስት ጊዜ አቻ ተለያይቷል። በ19ኙ ጨዋታዎች ላይ 36 ግቦችን ሲያስቆጥር 11 ጎሎች ተቆጥረውበታል።
ቡድኑ በ41 ነጥብ አራተኛ ደረጃን ይዟል።
በሊጉ ካከናወናቸው 19 ጨዋታዎች መካከል ስምንቱን ያሸነፈው ቦሌ ክፍለ ከተማ በበኩሉ አራት ጊዜ ሽንፈት አስተናግዷል። በቀሪ ሰባት ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርቷል። 23 ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ 18 ጎሎችን አስተናግዷል።
ቦሌ ክፍለ ከተማ በ31 ነጥብ ስድስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
መቻል ካሸነፈ ተከታታይ አራተኛ ድሉን ያስመዘግባል። የሶስተኝነት ደረጃን ከሃዋሳ ከተማ ይረከባል።
ባለፉት ሶስት የሊግ ጨዋታዎች ያላሸነፈው ቦሌ ክፍለ ከተማ ወደ አሸናፊነት መንገድ ይመለሳል።
ከቀኑ 7 ሰዓት ላይ ሲዳማ ቡና ከድሬዳዋ ከተማ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያከናውናሉ።
ሲዳማ ቡና በሊጉ 19 ጨዋታዎች አድርጎ ስምንት ጊዜ ድል ሲቀናው በተመሳሳይ ስምንት ጊዜ ተሸንፏል። በቀሪ ሶስት ጨዋታዎች አቻ ተለያይቷል። 19 ግቦችን ከመረብ ጋር ሲያገናኝ 24 ጎሎች ተቆጥረውበታል።
ቡድኑ በ27 ነጥብ ሰባተኛ ደረጃን ይዟል።
በውድድር ዓመቱ ካከናወናቸው 19 ጨዋታዎች ስድስቱን ያሸነፈው ድሬዳዋ ከተማ በ11ዱ ሽንፈት አስተናግዷል። በቀሪ ሁለት ጨዋታዎች ነጥብ ጥሏል።
በ19ኙ ጨዋታዎች 17 ግቦችን ሲያስቆጥር 30 ጎሎችን አስተናግዷል። ድሬዳዋ ከተማ በ20 ነጥብ ዘጠነኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ሲዳማ ቡና ካሸነፈ ሶስተኛ ተከታታይ ድሉን ያስመዘግባል።
ባለፉት አራት ጨዋታዎች ከድል የራቀው ድሬዳዋ ከተማ ወደ አሸናፊነት መንገድ ለመመለስ ይጫወታል።