ቀጥታ፡

40 ኪሎ ግራም ካናቢስ የተባለ አደንዛዥ ዕጽ በቁጥጥር ስር ዋለ

አዲስ አበባ ፤መጋቢት 11/2018 (ኢዜአ) :-በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሊተላለፍ የነበረ 40 ኪሎ ግራም ካናቢስ አደንዛዥ ዕጽ በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የአቪዬሽን ደኅንነት ባለሙያች በቁጥጥር ስር ውሏል፡፡

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ለኢዜአ በላከው መረጃ እንዳመለከተው፤ ከታይላንድ ባንኮክ ተነስቶ  ደቡብ አፍሪካ ጆሃንስበርግ መዳረሻው የሆነ አውሮፕላን በአዲስ አበባ  በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ትራንዚት ሲያደርገ በረቀቀ መልኩ በሻንጣ ውስጥ የተደበቀ 37 ነጥብ 6 ኪሎ ግራም የሚመዝን ካናቢስ አደንዛዥ ዕጽ በቁጥጥር ስር ውሏል፡፡ የእንግሊዝ ዜግነት ያለው  የአደንዛዥ ዕጹ አዘዋዋሪም ተይዞ ተጨማሪ ምርመራ እየተደረገበት ይገኛል፡፡

በተመሳሳይ ከፈረንሳይ ፓሪስ ወደ ኮሞሮስ ዋና ከተማ ሞሮኒ ሲጓዝ በነበረ አውሮፕላን ላይ በሻንጣ የውስጥ አካል ላይ በረቀቀ መልኩ የተደበቀ 3 ነጥብ 160 ኪሎ ግራም የሚመዝን የተባለ አደንዛዥ ዕጽ በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በትራንዚት በኩል ለማሳለፍ ሲሞከር በቁጥርር ስር ውሏል፡፡

አደንዛዥ ዕጾቹ በተዘረጋው ግልጽ የአሰራር ስርዓት አማካኝነት ከባለድርሻ አካላት ጋራ በመቀናጀት እና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመታገዝ በተከናወኑ ጥብቅ ፍተሻና ቁጥጥር መያዛቸውን መረጃው አመልክቷል፡፡

በተከታተይ ቀናት በቦሌ ዓለም-አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አደንዛዥ ዕጽ ለማስተላለፍ ሲደረጉ የነበሩ ሙከራዎች እንደወትሮው ሁሉ በሚከናወኑ ጥብቅ ፍተሸና የቁጥጥር ሥርዓቶች አለመሳካታቸውን ያስታወሰው አገልግሎቱ፤  የሀገርን ብሔራዊ ደኅንነትና የኢትዮጵያ አየር መንገድን መልካም ስምና ገጽታ የሚጎዱ መሰል ወንጀሎችን በከፍተኛ ዝግጁነትና በተደራጃ መንገድ የመከላከል እምጃዎቹ ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጧል፡፡

#Ethiopian_News_Agency #ኢዜአ #ENA

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም