ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መሪነቱን አጠናክሯል - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መሪነቱን አጠናክሯል
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 11/2018(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ የ20ኛ ሳምንት ሶስተኛ ጨዋታ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አዳማ ከተማን 6 ለ 0 በሆነ ሰፊ የግብ ልዩነት አሸንፏል።
በአበበ ቢቂላ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ረድኤት አስረሳኸኝ ሶስት ግቦችን በማስቆጠር ሀትሪክ ሰርታለች።
መሳይ ተመስገን ሁለት ግቦችን ከመረብ ላይ ስታሳርፍ እሙሽ ዳንኤል ቀሪዋን ጎል ለንግድ ባንክ አስቆጥራለች።
ሀትሪክ የሰራችው ረድኤት አስረሳኸኝ የጨዋታው ኮከብ በመባል ተመርጣለች።
በሊጉ 17ኛ ድሉን ያስመዘገበው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ነጥቡን ወደ 53 ከፍ በማድረግ መሪነቱን አጠናክሯል።
የወቅቱ የሊጉ አሸናፊ ንግድ ባንክ ከተከታዩ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ጋር ያለው ልዩነት ወደ ሁለት ነጥብ ከፍ አድርጓል።
በውድድር ዓመቱ ዘጠነኛ ሽንፈቱን ያስተናገደው አዳማ ከተማ በ21 ነጥብ ስምንተኛ ደረጃን ይዟል። ቡድኑ ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች አላሸነፈም።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንኳ ረድኤት አስረሳኸኝ በሊጉ ያስቆጠረችውን የግብ ብዛት ወደ 16 ከፍ በማድረግ 23 ግብ ያላትን የኢትዮ ኤሌክትሪኳ ዳግማዊት ሰለሞንን ትከተላለች።
ዛሬ በተደረጉ የ20ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ጨዋታዎች ሃዋሳ ከተማ ልደታ ክፍለ ከተማን 1 ለ 0 ሲያሸንፍ ሸገር ከተማ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ አንድ አቻ ተለያይተዋል።