ቀጥታ፡

ዒድ አል-ፈጥርን በጋራ በመሆን፣ በመረዳዳትና በመጠያየቅ የምናሳልፈው በዓል ነው

አምቦ፣ ነቀምቴ ፤መጋቢት 11/ 2018  (ኢዜአ)፦ ዒድ አል-ፈጥርን በጋራ በመሆን፣ በመረዳዳትና በመጠያየቅ እያሳለፉ መሆናቸውን የአምቦ ከተማ የእስልምና ሃይማኖት አባቶችና ተከታዮች ገለጹ። 

1447ኛው የዒድ አል-ፈጥር በዓል በዛሬው ዕለት በአምቦ ከተማ አስተዳደር በድምቀት ተከብሯል።   

በበዓሉ አከባበር ሥነ ሥርዓት ላይ የተገኙት የአምቦ ከተማ እስልምና ጉዳዮች ጸሐፊ አቶ አወል ሱልማን እንዳሉት፤ በረመዳን ወር የእስልምና ሃይማኖት በሚያዘው መሠረት የእምነቱ ተከታዮች በበጎ ተግባራት ላይ በትኩረት ሲሠሩ ቆይተዋል።   

ይህ የመረዳዳት ተግባር ከበዓሉ በኋላም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ገልጸዋል።   

አምቦ ከተማ ውስጥ የተለያዩ እምነት ተከታዮች በወንድማማችነትና በፍቅር ተከባብረው የሚኖሩ መሆናቸውን የጠቀሱት ጸሐፊው፤ በከተማው ያለው አብሮነት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።   

የአምቦ ከተማ ሃናን መስጂድ ዋና ኢማም ሼህ አልፊያ ከማል በበኩላቸው፤ እስልምና ፍቅርን፣ መቻቻልንና ሰላምን የሚሰብክ መሆኑን በማንሳት፤ ያለው የሌለውን በማገዝ እና የታመሙትን በመጠየቅ በዓሉን እያሳለፉ መሆኑን ገልጸዋል።   

መላው የእምነቱ ተከታዮች ይህንኑ በጎ ተግባር አጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስበዋል።  


 

በዓሉን በፍቅር፣ በሰላም በመተጋገዝ፣ ያለምንም ልዩነት ማሳለፍ እንደሚገባ የገለጹት ደግሞ ወይዘሮ አምና ኡስማን ናቸው።


  

የአምቦ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ባይሳ ጃላታ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ሙስሊሙ ማኅበረሰብ በረመዳን ወር ያሳየውን የመረዳዳት እሴት በቀጣይም ሰላምን በመጠበቅና በልማት ሥራዎች ላይ በመሳተፍ እንዲደግም ጥሪ አቅርበዋል።


 

በተመሳሳይ በነቀምቴ ከተማ ኢድ ሰላት ላይ የተገኙት የነቀምቴ ከተማ የእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ሰብሳቢ ሼህ ተማም መሐመድ፤ በከተማዋ ሙስሊም ማኅበረሰብ የመቻቻልና የመተሳሰብ እሴት በማጠናከር፣ ሰላምን በመጠበቅና በማስጠበቅ ረገድ የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።   

የነቀምቴ ከተማ ከንቲባ አቶ መሰረት ሀይሉ፤ የከተማው ሙስሊም ማኅበረሰብ በልማትና ሰላም በእኩልነት በመሳተፍ፣ በከተማዋ የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን ማስቀጠል ይገባል ብለዋል።

  
 

በዓሉ ሲከበርም አቅመ ደካሞችንና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ወገኖችን በማሰብ ሊሆን እንደሚገባ ከንቲባው አሳስበዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም