ሙስሊሙ ህብረተሰብ በረመዳን ወር ያሳየውን አንድነትና መተጋገዝ በልማትም ሊደግመው ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
ሙስሊሙ ህብረተሰብ በረመዳን ወር ያሳየውን አንድነትና መተጋገዝ በልማትም ሊደግመው ይገባል
ዲላ/ወላይታ ሶዶ፤ መጋቢት 11/2018(ኢዜአ)፦ የህብረተሰቡ የልማት ተሳትፎ ለዞኑ እድገት ወሳኝ በመሆኑ ሙስሊሙ በረመዳን ወር ያሳየውን አንድነትና መተጋገዝ በልማትም ሊደግመው እንደሚገባ የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዝናቡ ወልዴ(ዶ/ር) ገለጹ።
1447ኛው የዒድ አል ፈጥር በዓል በዲላ እና በወላይታ ሶዶ ከተሞች በተለያዩ ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች በድምቀት ተከብሯል።
በዓሉ በዲላ ስታዲየም ሲከበር የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዝናቡ ወልዴ(ዶ/ር) እንደገለጹት፣ የህብረተሰቡ የልማት ተሳትፎ ለዞኑ እድገት ወሳኝ በመሆኑ ሙስሊሙ ማህበረሰብ በረመዳን ወር ያሳያውን አንድነትና መተጋገዝ በዞኑ የልማት ሥራም መድገም እንዳለበት አስገንዝበዋል።
ያለው የሌለውን በማገዝ ማህበራዊ ሃላፊነትን ለመወጣት ሲከናወኑ የነበሩ ተግባራትን በቀጣይም በማጠናከር ለዞኑ ሰላምና እድገት ድጋፉን እንዲያጠናክር ጥሪ አቅርበዋል።
የዲላ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ መስፍን ደምሴ(ዶ/ር) በበኩላቸው የእምነቱ ተከታዮች የረመዳን ወርን በጸም፣ ጸሎትና መልካም ተግባራትን በማከናወን ማሳለፋቸውን ገልጸዋል።
የሀይማኖቱን አስተምህሮ ከመፈጸም ባለፈ የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳትና ማዕድ በማጋራት የፈጸሙት ተግባር በከተማው የህብረተሰቡን አብሮነት ለማጎልበት ሚናው የላቀ ነው ብለዋል።
የረመዳን ወር ከጾምና ከጸሎት ባሻገር በበጎ ሥራም ጎልተን የታየንበት ነው ያሉት ደግሞ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ኡላማዎች ምክር ቤት ምክትል ሰብሳቢና የዲላ ከተማ ቢላል መስጅድ ዋና ኢማም ሼህ ሰኢድ መሐመድ ናቸው።
በተለይ በመደጋገፍና በልማት ሥራዎች የታየውን ተሳትፎ በመልካምነት አንስተው ይህም በቀጣይ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።
በተመሳሳይ ዜና የዒድ አል ፈጥር በዓል በወላይታ ሶዶ ከተማም በድምቀት ተከብሯል።
በከተማው የቢላል መስጂድ ዋና ኢማም ሼህ ሸረፈዲን መሐሙድ ጾሙን ለሀገር ሰላምና አንድነት በመጸለይና የተቸገሩ ወገኖችን በመደገፍ በአብሮነት ማሳለፋቸውን ተናግረዋል።
ዛሬም በዓሉን ከሌሎች እምነት ተከታዮች ጋር በአንድነትና በደስታ እያሳለፉ መሆናቸውን ገልጸው፣ ይህም ፍቅርና መተሳሰብን ያጠናክራል ብለዋል።
በጾሙ ወቅትና በዒድ በዓል የተቸገሩትን ለመርዳት ያሳየነውን ትጋት የሁሌም ልናደርገው ይገባል ሲሉም አሳስበዋል።
በሥራ ጉዳይ ወደ ኢትዮጵያ ከመጡ ሦስት ዓመት እንደሆናቸው የተናገሩት ፓኪስታናዊው ሙኔብ ሙሽታቅ በበኩላቸው ኢትዮጵያውያን የሰጡን ፍቅር በዓሉን በደስታና በአብሮነት ለማሳለፍ አስችሎናል ብለዋል።
የኢትዮጵያውያን እንግዳ ተቀባይነትና አክብሮት እንደ ሀገራችው በነፃነት እንዲንቀሳቀሱ ከማድረጉ በላይ ቤተሰባዊነት እንዲሰማቸው ማድረን ተናግረዋል።
ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ ወይዘሮ ፈይሩዛ ሰማን በረመዳን ወር ከጥላቻና መሰል ተግባራት ጭምር በመራቅ በህዝቡ ዘንድ ሰላምና ፍቅር እንዲጎለብት ያከናወኗቸውን ተግባራት በቀጣይም እንደሚያጠናክሩ ገልጸዋል።
ዘንድሮ በጾም ወቅም ሆነ በዒድ በዓል በተለይ ከክርስቲያን ወገኖቻችን ጋር የነበረን አብሮነት ኢትዮጵያዊነታችንን አድምቆታል ያሉት ወይዘሮዋ፣ ይህንን ልምድ ማስቀጠል ለአብሮነታችን መጠናከር ወሳኝ ነው ብለዋል።