ቀጥታ፡

በረመዳን የፆም ወር የታየው የመርዳትና የማገዝ እሴት ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል - የእምነቱ ተከታዮች

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 11/2018(ኢዜአ)፦ በረመዳን የፆም ወር የታየው አቅመ ደካማና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ዜጎችን የመርዳትና የማገዝ እሴት ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ የእምነቱ ተከታዮች ገለጹ።

የዒድ አል-ፈጥር በዓልን የእስልምና እምነት በሚያዘው የመረዳዳትና አብሮነት ኃይማኖታዊ ዕሴት እያሳለፉ እንደሚገኙ የእምነቱ ተከታዮች ተናግረዋል።


 

የ1447ኛው የዒድ አል-ፈጥር በዓል በእምነቱ ተከታዮች ዘንድ በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች ከማለዳው ጀምሮ በታላቅ ድምቀት ተከብሯል።

በአዲስ አበባ ከተማም በርካታ የእስልምና እምነት ተከታዮች በስታዲየም በመሰባሰብ ኃይማኖታዊ ስርዓቱ በሚያዘው መሰረት በታላቅ ድምቀት አክብረዋል።

በክብረ በዓሉ ላይ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሸህ ሐጂ ኢብራሒም ቱፋን ጨምሮ በርካታ የእምነቱ ተከታዮች ታድመዋል።

አስተያታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የበዓሉ ታዳሚዎች እንዳሉት፤ የረመዳን ወር መረዳዳትና መደጋገፍ ጎልቶ የታየበት ወቅት መሆኑንና ይህም ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው ተናግረዋል።

ከበዓሉ ታዳሚዎች መካከል ወጣት መሐመድ ቡሽራ፤ በረመዳን ወር የነበረው መረዳዳትና መደጋገፍ በዒድ-አልፈጥር በዓልም ያለው ለሌለው በማካፈል በጋራ እንደሚያከብሩት ገልጿል።

የዒድ አል-ፈጥር በዓል ሲከበር ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ወገኖች በማሰብና ያለው ለሌለው በማካፈል በደስታ ማሳለፍ እንደሚያስፈልግ ተናግሯል።

በረመዳን የፆም ወር የታየው የአቅመ ደካማና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ዜጎችን የመርዳትና መተጋገዝ ባህል ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አስገንዝቧል።


 

ሌላኛው የበዓሉ ታዳሚ ሺህ መከታ ሙሔ በበኩላቸው፤ የረመዳን ወር ህዝበ ሙስሊሙ ፈጣሪውን በማሰብ የሚያሳልፈው የእዝነትና የመተጋገዝ ወቅት ነው ብለዋል።

የዒድ አል-ፈጥር በዓልም የኃይማኖቱ ሥርዓት በሚያዘው መሠረት በመረዳዳትና በአንድነት ከጎረቤት፣ ከአቅመ ደካሞችና ዝቅተኛ ገቢ ካላቸው ወገኖች ጋር በታላቅ ደስታ የሚከበር መሆኑን ገልጸዋል።


 

የእስልምና እምነት መሰረቱ መተጋገዝና ሰላም በመሆኑ የዒድ አል-ፈጥር በዓልንም በአንድነትና በመተጋገዝ እናከብራለን ያሉት ደግሞ ኑርሰቡ አብደላ ናቸው።


 

ወጣት አብዱራህማን ሒርጶ በበኩሉ፤ በዒድ አል-ፈጥር በዓል ከወዳጅ ዘመዶቹ ባሻገር ከሌሎች የእምነቱ ተከታይ ጓደኞቹ ጋር ጭምር በደስታና በፍቅር እንደሚያከብሩት ገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም