ቀጥታ፡

ህዝበ ሙስሊሙ በረመዳን ወር ያሳየውን መረዳዳትና መተጋገዝ በበዓሉ እለትና ከዚያ በኋላም ሊያጠናክረው ይገባል

ባህርዳር፤ መጋቢት 11/2018(ኢዜአ)፦ ህዝበ ሙስሊሙ በረመዳን ወር ያሳየውን መረዳዳትና መተጋገዝ በበዓሉ እለትና ከዛ በኋላም አጠናክሮ ሊያስቀጥለው እንደሚገባ የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት አስገነዘበ።

‎ህዝበ ሙስሊሙ የአድ አልፈጥር በዓልን ሲያከብር የተቸገሩ ወገኖችን ካለው በማካፈልና የነበረ የአብሮነት እሴቱን በማጠናከር ሊሆን ይገባልም ብሏል ከፍተኛ ምክር ቤቱ።


 

1447ኛው የኢድ አልፈጥር በዓል በባህር ዳር ከተማ ሃይማኖታዊ እሴቱን በጠበቀ መልኩ ዛሬ በድምቀት ተከብሯል።

‎የምክር ቤቱ ምክትል ፕሬዚዳንት ሼኽ መሀመድ ኢብራሂም ባስተላለፉት መልዕክት ምእመኑ በረመዳን ወር ያሳየውን መረዳዳትና መተጋገዝ በበዓሉ እለትና በቀጣይም አጠናክሮ ሊያስቀጥል ይገባል ብለዋል።

የሀገራችንን ሰላም አፅንተን ለማዝለቅና ልማቱን ለማፋጠን አንድነታችንን ከመቸውም ጊዜ በበለጠ ልናጠናክር ይገባል ሲሉም ገልጸዋል።

‎የተቸገሩትን ከመደገፍና ከመርዳት ባለፈ የአካባቢያችንን ሰላም ነቅተን በመጠበቅ በዓሉን በአብሮነት መንፈስ ማክበር አለብን ብለዋል በመልዕክታቸው።


 

የባህርዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው በበኩላቸው እንደገለጹት ሙስሊሙ ማህበረሰብ የከተማው ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥና ልማቱ እንዲፋጠን ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክቷል።

መንግስት ችግሮችን ለመቅረፍ እያደረገ ያለው ጥረት ዳር እንዲደርስ ሙስሊሙ ማህበረሰብ የጀመረውን ድጋፍና አጋርነት አጠናክሮ ሊያስቀጥል ይገባል ብለዋል።

አቶ ሙሃባው አብዲ እና ወጣት ሃብቴ ጋሹ የተባሉ የበዓሉ ታዳሚያን እንዳሉት፤ በዓሉን የምናከብረው አንድነትና አብሮነትን ከማጠናከር ጎን ለጎን የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳትና በማገዝ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም