ቀጥታ፡

በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሴቶች ጠንካራ ተሳትፎ የሚያደርጉበት እንዲሆን የተቀናጀ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው 

ባህር ዳር፤ መጋቢት 11/2018(ኢዜአ) ፦ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሴቶች ጠንካራ ተሳትፎ የሚያደርጉበት እንዲሆን የተቀናጀ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ ሴቶች ፌዴሬሽን ገለጸ።
 
ፌዴሬሽኑ በአማራ ክልል ለሚገኙ የሴቶች ፌዴሬሽን አመራሮችና አባላት ለሁለት ቀናት የሚቆይ የምርጫ ታዛቢነት የአሰልጣኞች ሥልጠና በባህር ዳር ከተማ ዛሬ አስጀምሯል።

የኢትዮጵያ ሴቶች ፌዴሬሽን ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ገነት ስዩም በሥልጠናው ላይ እንደገለጹት፤ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ፌዴሬሽኑ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ ይገኛል።

የምርጫ ሂደቱን ሰላማዊ ከማድረግ ጎን ለጎንም፣ ሴቶች በምርጫው በታዛቢነት በመሳተፍ ድርብ ሀገራዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ለማስቻል እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።

የፌዴሬሽኑ አባላት ገለልተኛነታቸውን ጠብቀው የታዛቢነት ሚናቸውን በአግባቡ እንዲወጡ የአሰልጣኞች ሥልጠና መሰጠት መጀመሩን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሯ፤ ሥልጠናው በምርጫ ሥነ ምግባር፣ መርሆዎችና በታዛቢነት ሚና ላይ ያተኮረ መሆኑን ጠቁመዋል።

የአማራ ክልል ሴቶች ማኅበራት ፌዴሬሽን ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ እንየ ገነቱ በበኩላቸው፤ ሰልጣኞች የሚያገኙትን ዕውቀት ለወረዳ በጎ ፈቃደኛ ሴት ታዛቢዎች ማስጨበጥ እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል።

ታዛቢዎቹ ከፖለቲካ ወገንተኝነት ነጻ የሆኑ፣ በትምህርታቸውና በልምዳቸው ብቁ የሆኑ እንዲሁም አካል ጉዳተኞችን ያካተቱ ሆነው መመልመላቸውን ተናግረዋል።

የሰሜን ጎንደር ዞን ሴቶች ማኅበራት ፌዴሬሽን ሥራ አስፈጻሚ ወይዘሮ ዝማማ አቡሃይ እንደገለጹት፤ ምርጫው ፍትሃዊና ገለልተኛ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ተዘጋጅተዋል።

ፌዴሬሽኑ ከዚህ ቀደም በሐዋሳ፣ በጅማ፣ በአፋርና በደሴ ከተሞች ተመሳሳይ የታዛቢዎችና የአሰልጣኞች ሥልጠና መስጠቱን አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም