ቀጥታ፡

ከንቲባ አዳነች አቤቤ የኢድ አል-ፈጥር በዓልን በማስመልከት በተስፋ ብርሃን የምገባ ማዕከላት ማዕድ አጋሩ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 11/2018(ኢዜአ)፦ የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ 1447ኛው የኢድ አል-ፈጥር በዓልን በማስመልከት በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ እና በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ በሚገኙ የተስፋ ብርሃን የምገባ ማዕከላት ማዕድ አጋርተዋል።

1447ኛው የኢድ አል-ፈጥር በዓል በእምነቱ ተከታዮች ዘንድ እየተከበረ ይገኛል።


 

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዓሉን ምክንያት በማድረግ በመዲናዋ በሁሉም ክፍለ ከተሞች በሚገኙ 28ቱም የተስፋ ብርሃን የምገባ ማዕከላት አቅመ ደካሞችን፣ አካል ጉዳተኞችን፣ አረጋውያንና ለከፋ ማህበራዊ ችግር ተጋላጭ ለሆኑ ወገኖቻችንን ማዕድ የማቋደስ መርሃ ግብር መከናወኑን ገልጸዋል።

ከንቲባዋ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ እና በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ በሚገኙ የተስፋ ብርሃን የምገባ ማዕከላት በመገኘት ማዕድ በማቋደስ እንኳን አደረሳችሁ ማለታቸውን ተናግረዋል።


 

ማዕከላቱ በዐቢይ ጾም እና በረመዳን ወቅትም ጭምር ለጾመኞች እንደየ እምነታቸው የአፍጥር እና የፆም ምገባ አገልግሎት ሲሰጡ መቆየታቸውን አውስተዋል።

የተደረገውን ጥሪ በመቀበል በማዕከላቱ ምገባ እያደረጉ ለሚገኙ ባለሀብቶች፣ አጋሮችና አስተባባሪዎች በተጠቃሚዎቹ ስም ከልብ የመነጨ ምስጋናዬን ለማቅረብ እወዳለሁ ብለዋል።

ከንቲባዋ በዓሉ የደስታና አብሮነት የሚጎለብትበት እንዲሆንም ተመኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም