ቀጥታ፡

የነዋሪዎችን የአብሮነትና መረዳዳት ባህል የሚያጎለብቱ ሰው ተኮር ፕሮጀክቶችን በአጭር ጊዜ ማሳካት ተችሏል - ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 11/2018(ኢዜአ)፦ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን የአብሮነትና መረዳዳት ባህል የሚያጎለብቱ ሰው ተኮር ፕሮጀክቶችን በአጭር ጊዜ ማሳካት እንደተቻለ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

1447ኛው የዒድ አል-ፈጥር በዓል በእምነቱ ተከታዮች ዘንድ በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች በታላቅ ድምቀት በአደባባይ ተከብሯል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም የዒድ አል-ፈጥር በዓልን ምክንያት በማድረግ በተስፋ ብርሃን የምገባ ማዕከላት በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች የማዕድ ማጋራት መርሃ ግብር አካሂዷል።


 

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ በሚገኘው 6ኛው እና በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ 21ኛው የተስፋ ብርሃን የምገባ ማዕከላት በመገኘት ማዕድ አጋርተዋል።

ከንቲባ አዳነች በዚሁ ወቅቱ ለእምነቱ ተከታዮች ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳቹ መልዕክት እንደገለጹት፤ በከተማዋ ከጊዜ ወደ ጊዜ በህብረተሰቡ ዘንድ አብሮነትና የመረዳዳት ባህል እየጎለበተ መጥቷል።

ለአብነትም በዘንድሮው የረመዳንና የ1447ኛው የዒድ አል-ፈጥር በዓል በመዲናዋ ነዋሪዎች ዘንድ የእርስ በእርስ መረዳዳትና አብሮነት ደምቆ እንደታየ ተናግረዋል።

መረዳዳትና አንድነት በሚጎላበት የረመዳን ወር ማጠናቀቂያ በሆነው የዒድ አል-ፈጥር በዓልን ምክንያት በማድረግ በተለያዩ የምገባ ማዕከላት የማዕድ ማጋራት መርሃ ግብር መካሄዱን አንስተዋል።

በኢትዮጵያ ሀገራዊ ለውጥ ማግስትም የመዲናዋን ነዋሪዎች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ውጤታማ ሰው ተኮር የልማት ፕሮጀክቶች በአጭር ጊዜ መገንባታቸውን ገልጸዋል።

የመዲናዋን ነዋሪዎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በተደረገው ጥረት የድርሻቸውን ለተወጡ ባለሃብቶችና የልማት አጋሮች ምስጋና አቅርበዋል።


 

በቀጣይም የመዲናዋ ነዋሪዎች በሁሉም መስክ የመረዳዳትና የአብሮነት ባህልና ዕሴቶችን አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የምገባ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ፀዳለች ሚካኤል፤ በመዲናዋ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ በርካታ ወገኖች በሰው ተኮር የምገባ ማዕከላት የምገባ አገልግሎት እየተሰጠ ነው ብለዋል።

የዒድ አል-ፈጥር በዓልን ምክንያት በማድረግ በ28 የምገባ ማዕከላት ከ30ሺህ 600 በላይ ለሚሆኑ የእምነቱ ተከታዮች የማዕድ ማጋራት መርሃ ግብር መካሄዱን አስታውቀዋል።

የእምነቱ ተከታዮችም፤ የዒድ አል-ፈጥር በዓልን ምክንያት በማድረግ ከተማ አስተዳደሩ ባዘጋጀው የማዕድ ማጋራት መርሃ ግብር ለተደረገላቸው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

የማዕድ ማጋራት መርሃ ግብሩ የዜጎችን አብሮነትና የመረዳዳት ባህል በማጎልበት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም