ሙስሊሙ ማህበረሰብ ለዘመናት ያጎለበተውን በሰላም አብሮ የመኖርና የማደግ መልካም እሴቶች ማስቀጠል አለበት - ኢዜአ አማርኛ
ሙስሊሙ ማህበረሰብ ለዘመናት ያጎለበተውን በሰላም አብሮ የመኖርና የማደግ መልካም እሴቶች ማስቀጠል አለበት
ቦንጋ/ሚዛን አማን ፤መጋቢት 11/2018 (ኢዜአ)፡- ሙስሊሙ ማህበረሰብ ለዘመናት ያጎለበተውን በሰላም አብሮ የመኖርና የማደግ መልካም እሴቶች ለቀጣይ ትውልድ ጠብቆ ማቆየትና ማስተላለፍ እንዳለበት ተገለጸ።
በረመዳን የጾም ወቅት የታየው በጎ ተግባርን በማጠናከር ሰላምና አንድነትን ማስቀጠል እንደሚገባም ተመላክቷል።
1ሺህ 447ኛ የዒድ አል ፈጥር በዓል በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል በቦንጋ እና በሚዛን አማን ከተሞች ተከብሯል።
በቦንጋ ከተማ በዓል ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የከተማው ከንቲባ ተክለዓብ ቡሎ (ዶ/ር) ሙስሊሙ ማህበረሰብ ከሌሎች ጋራ በሰላምና በመከባበር አብሮ የመኖርና የማደግ ባህልን አዳብሯል።
ለሀገር ሰላምና እድገት መጠናከር ጉልህ ፋይዳ ያለውን ይሄን የአብሮነት እሴቱን ጠብቆ ማቆየትና ለቀጣይ ትውልድ ማስተላለፍ እንዳለበት ተናግረዋል።
ለሀገር ሰላምና ልማት መፅናት የሚያበረክተውን አስተዋጾም አጠናክር መቀጠል እንዳለበት አስገንዝብዋል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ሥራ አስፈፃሚ ሐጂ መሐመድ ጅብሪል በበኩላቸው የረመዳን ወር የመረዳዳትና የመተጋገዝ እሴት የሚጎላበት መሆኑን ጠቅሰው የዒድ በዓልንም በመደጋገፍ ልናከብረው ይገባል ብለዋል።
እስልምና የሰላም ምልክት መሆኑን ጠቅሰው፣ ህዝበ ሙስሊሙ በረመዳን ወቅት ያሳየውን በጎ ተግባር በማስቀጠል ሰላምና አብሮነቱን ማጠናከር እንዳለበት አሳሰበዋል።
በከተማው የዳሩ ሰላም መስጂድ ኢማም ሼህ መሐመድ አማን "የረመዳን ወር ከአላህ ጋር ብቻ ሳይሆን ከሰው ልጆች ጋርም እንዴት በሰላምና በፍቅር መኖር እንደምንችል በተግባር የምናሳይበት ቅዱስ ወር ነው" ብለዋል።
የበዓሉ ተሳታፊ ወይዘሮ ዘምዘም ኑሩ የፆሙን ወቅት ካላቸው የተቸገሩትን በመደገፍና በመረዳዳት ማሳለፋቸውን ገልፀው፣ ይህን መልካም ተግባር በዒድ በዓልና በቀጣይም እንደሚያጠናክሩ ተናግረዋል።
በሚዛን አማን ከተማ በዓሉ ሲከበር የተገኙት የቤንች ሸኮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሀብታሙ ካፍትን በበኩላቸው እንዳሉት የዒድ አል ፈጥር በዓል ያለው ለሌለው በማካፈል መተጋገዝ የሚጎላበት ነው።
ለአካባቢው ልማትና ዘላቂ ሰላም መስፈን ሕዝበ ሙስሊሙ እያበረከተ ያለውን አስተዋጽኦ የጎላ መሆኑንና ይህንንም አጠናክሮ ማስቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል።
የቤንች ሸኮ ዞን እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ፀሐፊ አቶ ዑመር ሙስጠፋ ባስተላለፉት መልዕክት የእዝነት ወር በሆነው ረመዳን የፈጸምናቸውን መልካም ተግባራት በቀጣይም አጠናክረን ልንቀጥል ይገባል ብለዋል።
መዋደድ፣ መተጋገዝና መተባበር ፍቅርና አንድነትን ለማጠናከር ትልቅ ሚና ስላለው በእስልምና አስተምህሮ መሠረት እነዚህን መልካም ተግባራትን አጥብቆ መያዝ ይገባል ሲሉ አስገንዝበዋል።
የተሻለ ነገን ለመፍጠር በሚደረጉ ጥረቶች ሙስሊሙ ለሀገር ሰላምና ልማት ከመንግስት ጋር በመቀራረብ ሲያበረክት የቆየውን አስተዋጾ ማስቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል።
ከበዓሉ ታዳሚዎች መካከል አቶ እስማኤል ኑራ የረመዳን ወርን በጾም፣ በዱዓ እና አቅመ ደካሞችን በመርዳት በጥሩ ሁኔታ ማሳለፋቸውን ገልጸዋል።
አብሮነትን ለማጽናት የዛሬው የዒድ አልፈጥር በዓልንም ከሙስሊም እና ክርስቲያን ወንድሞቻችን ጋር በመጠያየቅ እያከበርነው እንገኛለን ብለዋል።
የደስታ በዓል የሆነውን ዒድ አል ፈጥርን ስናከብር ያለ ምንም ልዩነት የተቸገሩትን በመርዳትና በማስደሰት እያከበሩ መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ አቶ ነዝፍ ጀማል ናቸው።
ወይዘሪት ሀያት እንዲሪስ በበኩላቸው ሃይማኖታዊ መልካም ዕሴቶቻችን ለማኅበራዊ መሠረቶቻችን ያላቸውን በጎ ተጽዕኖ ለማሳደግ የረመዳን ወር ትሩፋቶችን እናጠናከራልን ሲሉ ገልጸዋል።