ቀጥታ፡

ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በተከናወኑ ተግባራት ኢንቨስትመንት የመሳብ አቅም አድጓል

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 11/2018(ኢዜአ)፦ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ ኢንቨስትመንትን ምቹ ለማድረግ በተከናወኑ ተግባራት ኢንቨስትመንት የመሳብ አቅም ማደጉን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ እና ሶማሌ ክልሎች የዘርፉ የስራ ሀላፊዎች ገለጹ።

መንግሥት ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ የኢኮኖሚ ሪፎርም በማድረግ ኢትዮጵያን ለኢንቨስትመንት ምቹ የሚያደርጉ ተግባራትን አከናውኗል።

የኢንቨስትመንት ፈቃድ አሰጣጥ ማሻሻያ፣ ዲጂታል አሰራርን ማስፋት፣ የህግ ማዕቀፎችን ማሻሻል እና ለንግድ ስራው ማነቆ የሆኑ የአሰራር ስርዓት ሰንሰለቶች ርዝመትን የሚቀርፉ በርካታ ሪፎርሞች ተደርገዋል።

ለኢንቨስተሮች የአገልግሎት አሰጣጥን ለማዘመንና መሰረተ ልማትን በሚገባ ለማሟላት የተከናወኑ ተግባራት ኢትዮጵያን ተመራጭ የኢንቨስትመንት መዳራሻ እያደረጋት ይገኛል።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አባስ መሀመድ(ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ተግባራዊ የተደረገው የኢኮኖሚ ሪፎርም ኢንቨስትመንትን በመሳብ ረገድ ትልቅ ሚና እየተጫወተ ነው።

በክልሉ በተያዘው በጀት ዓመት ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ 146 ባለኃብቶች በተለያዩ መስኮች ለመሰማራት መሬት መውሰዳቸውንና ኢንቨስት ለማድረግ በዝግጅት ላይ እንደሚገኙ አመልክተዋል።

ወደ ክልሉ የሚመጣው የኢንቨስትመንት ፍሰት እየጨመረ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህም የሀገራዊ የኢኮኖሚ ሪፎርሙ ውጤት ነው ብለዋል።

በክልሉ ኢንቨስትመንትን የሚያበረታቱ አሰራሮች እየተተገበሩ መሆኑን ጠቁመው፤ መሬትን ባነሰ የሊዝ ዋጋ ማቅረብን ጨምሮ ክልሉ ለኢንቨስትመንት ያለውን እምቅ አቅም በሰፊው የማስተዋወቅ ሥራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ለኢንቨስትመንቱ በተፈጠረው ምቹ ምህዳር የሥራ ዕድል ፈጠራ ላይም ተጨባጭ ውጤቶች እንዲገኝ አስችሏል ነው ያሉት።

የሶማሌ ክልል የኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር አህመድ ረሺድ በበኩላቸው፤ በክልሉ በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ በሆቴልና ቱሪዝምን ጨምሮ በተለያዩ መስኮች ለኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታ የመፍጠሩ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል።

በተያዘው በጀት ዓመት በምግብ ማቀነባበር፣ በግብርና፣ በእንስሳት መኖ አቅርቦት፣ ሪል ስቴትን ጨምሮ በተለያዩ መስኮች ባለኃብቶች ኢንቨስት ማድረጋቸውን ጠቁመዋል።

ከለውጡ በኋላ በክልሉ የሰፈነው ሠላም እንዲሁም ኢንቨስትመንት ምቹ ማድረግ ላይ የተሰሩ ሥራዎች ውጤት ማምጣታቸውንም አብራርተዋል።

በዚህም በክልሉ ለባለኃብቶች አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ በተለያዩ መስኮች እንዲሰማሩ መደረጉን ለአብነት አንስተዋል።

በክልሉ ኢንቨስት የሚያደርጉ ባለኃብቶች ከፋይናንስ፣ ከመሰረተ ልማት አቅርቦት እና ሌሎች አገልግሎቶች የሚገጥማቸውን ችግሮች ለመፍታት ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

ክልሉ በኢንቨስትመንት በኩል ያሉትን አቅሞች አሟጦ ለመጠቀም የሚያደርገው ጥረት በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም