የሴቶች ፕሪሚየር ሊግ የ20ኛ ሳምንት ተጠባቂ ጨዋታዎች - ኢዜአ አማርኛ
የሴቶች ፕሪሚየር ሊግ የ20ኛ ሳምንት ተጠባቂ ጨዋታዎች
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 11/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ 20ኛ ሳምንት ዛሬ ይጀመራል።
በዕለቱ ሶስት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።
ከረፋዱ 9 ሰዓት ላይ አዳማ ከተማ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ይጫወታሉ።
አዳማ ከተማ በሊጉ ካደረጋቸው 19 ጨዋታዎች መካከል አምስቱን ሲያሸንፍ በስምንቱ ተሸንፏል። በስድስት ጨዋታዎች አቻ ወጥቷል።
በ19ኙ ጨዋታዎች ላይ 14 ግቦችን ሲያስቆጥር 28 ጎሎችን አስተናግዷል። ቡድኑ በ21 ነጥብ ስምንተኛ ደረጃን ይዟል።
ተጋጣሚው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በበኩሉ በውድድር ዓመቱ 19 ጨዋታዎችን አድርጎ 16 ጊዜ ድል ሲቀናው የተሸነፈው አንድ ጊዜ ብቻ ነው። በቀሪ አምስት ጨዋታዎች አቻ ወጥቷል።
52 ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ ሰባት ጎሎችን አስተናግዷል።
የወቅቱ የሊጉ አሸናፊ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ50 ነጥብ ሊጉን እየመራ ነው። ንግድ ባንክ በሊጉ በርካታ ግቦችን ያስቆጠረ እና አነስተኛ የጎል መጠን ያስተናገደ ቡድን ነው።
በ19ኛ ሳምንት ከቦሌ ክፍለ ከተማ አንድ አቻ የተለያየው አዳማ ከተማ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይጫወታል።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ካሸነፈ የሊጉን መሪነት ያጠናክራል።
በሌላኛው መርሐ- ግብር ሸገር ከተማ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ከቀኑ 7 ሰዓት በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ሸገር ከተማ በሊጉ ባካሄዳቸው 19 ጨዋታዎች 12 ጊዜ ሲያሸንፍ አምስተኛ ጊዜ ተሸንፏል። በቀሪ ሁለት ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርቷል። በ19ኙ ጨዋታዎች ላይ 32 ግቦችን ሲያሳርፍ 19 ጎሎች ተቆጥረውበታል። ቡድኑ በ38 ነጥብ አምስተኛ ደረጃን ይዟል።
ኢትዮ ኤሌክትሪክ በሊጉ 19 ጨዋታዎችን አድርጎ በ16ቱ አሸንፎ በአንዱ ተሸንፎ በሁለቱ አቻ ወጥቷል። 43 ግቦችን ሲያስቆጥር 10 ጎሎች ገብተውበታል።
ቡድኑ በ50 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዟል።
በ19ኛ ሳምንት ከድሬዳዋ ከተማ ጋር አንድ አቻ የወጣው ሸገር ከተማ ወደ አሸናፊነት መንገድ ለመመለስ ይጫወታል።
ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ19ኛ ሳምንት ከሃዋሳ ከተማ ጋር ያለ ግብ አቻ መለያየቱን ተከትሎ የሊጉን መሪነት ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አስረክቧል።
ማሸነፍ ኢትዮ ኤሌክትሪክ በዋንጫ ፉክክሩ ወሳኝ ሶስት ነጥብ እንዲያገኝ ያስችለዋል።
ከረፋዱ አራት ሰዓት ላይ ሃዋሳ ከተማ ከልደታ ክፍለ ከተማ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ጨዋታውን ያደርጋል።
ሃዋሳ ከተማ በሊጉ 19 ጨዋታዎችን በማድረግ 11ዱን ሲያሸንፍ በሁለቱ ተሸንፏል። ስድስት ጊዜ ነጥብ ተጋርቷል። በጨዋታዎቹ ላይ 33 ግቦችን ሲያስቆጥር 12 ጎሎች ተቆጥረውበታል። ቡድኑ በ39 ነጥብ አራተኛ ደረጃን ይዟል።
ተጋጣሚው ልደታ ክፍለ ከተማ በውድድር ዓመቱ ካደረጋቸው 19 ጨዋታዎች በአራቱ ድል ሲቀናው 12 ጊዜ ተሸንፏል። በሶስቱ ጨዋታዎች አቻ ወጥቷል። 21 ግቦችን ከመረብ ጋር ሲያገናኝ 39 ግቦችን አስተናግዷል። ቡድኑ በ15 ነጥብ 10ኛ ላይ ተቀምጧል።
በ19ኛ ሳምንት ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ያለ ግብ አቻ የተለያየው ሃዋሳ ከተማ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይጫወታል።
ባለፉት ሶስት የሊግ ጨዋታዎች ከድል የራቀው ልደታ ክፍለ ከተማ ካሸነፈ ወደ ድል መንገድ ይመለሳል።
የዛሬ ጨዋታዎች በዋንጫ ፉክክሩ ወሳኝ የሚባሉ ናቸው።
የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ 20ኛ ሳምንት እስከ መጋቢት 13 ቀን 2018 ዓ.ም ይቆያል።
የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱን የኢትዮ ኤሌክትሪኳ ዳግማዊት ሰለሞን በ22 ግቦች እየመራች ነው። የኢትዮጵያ ንግድ ባንኳ ረድኤት አስረሳኸኝ በ13 ጎሎች ትከተላለች።