21ኛ የዓለም የቤት ውስጥ ዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ዛሬ ይጀመራል - ኢዜአ አማርኛ
21ኛ የዓለም የቤት ውስጥ ዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ዛሬ ይጀመራል
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 11/2018 (ኢዜአ)፦ 21ኛው የዓለም አትሌቲክስ የቤት ውስጥ (World Athletics Indoor Championship) ዛሬ በፖላንድ ቶሩን ከተማ ይጀመራል።
በውድድሩ ላይ ከ118 ሀገራት የተወጣጡ 674 አትሌቶች ይሳተፋሉ። ከነዚህም ውስጥ 345 ወንድ እና 329 ሴት አትሌቶች ናቸው።
ኢትዮጵያም በሻምፒዮናው ላይ በስድስት አትሌቶች እንደምትወከል የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።
ብርቄ ኃየሎም፣ ጌትነት ዋለ፣ ንግስት ጌታቸው፣ ፍሬወይኒ ኃይሉ፣ ባለሽኝ ባወቀ እና አዲስ ይሁኔ ናቸው።
አትሌቶቹ በ800 እና 3000 ሜትር ውድድሮች ላይ ይሳተፋሉ።
የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን ከአትሌቶቹ በተጨማሪ አንድ ቡድን መሪ፣አንድ የቴክኒክ ቡድን መሪ እና አንድ አሰልጣኝ አካቷል።
ሻምፒዮናው እስከ መጋቢት 13 ቀን 2018 ዓ.ም የሚቆይ ሲሆን በሁለቱም ጾታዎች በተመሳሳይ 13 በድምሩ 26 የወርቅ ሜዳሊያ የሚያስገኙ ውድድሮች ይካሄዳሉ።
በ20ኛው የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና የወርቅ ሜዳሊያ ያገኙ አትሌቶች ድላቸውን ለማስጠበቅ በዘንድሮ ውድድር ላይ ይሳተፋሉ።
ኢትዮጵያ እ.አ.አ በ2025 በቻይና ናንጂንግ በተካሄደው 20ኛው የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ሁለት የወርቅ እና ሶስት የብር በድምሩ አምስት ሜዳሊያዎችን በማግኘት ሶስተኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቁ የሚታወስ ነው።
ኢትዮጵያ በሻምፒዮናው ላይ ስትሳተፍ የአሁኑ ለ19ኛ ጊዜ ነው። ከዚህ ቀደም በነበራት 18 ተሳትፎዎቿ 35 የወርቅ ፣ 17 የብር እና 15 የነሐስ በአጠቃላይ 67 ሜዳሊያዎችን አግኝታለች።