ለነዋሪዎቿ ምቾትን የፈጠረው የአዲስ አበባ አዲሱ ገጽታ - ኢዜአ አማርኛ
ለነዋሪዎቿ ምቾትን የፈጠረው የአዲስ አበባ አዲሱ ገጽታ
አዲስ አበባ እየተዋበች፤ እየደመቀች ነው። ለተሽከርካሪዎች ብቻ ሳይሆን ለእግረኞችም ምቹና ሰፋፊ ጎዳና ገንብታለች። ይህን የስልጡንነት አክሊል የተቀዳጀችው ይህች መዲና ልክ እንደ ስሟ መልክና ግብሯ አጊጧል።
ዛሬ ላይ የመዲናዋ አውራ ጎዳናዎች በግራና በቀኝ በእግረኛ መንገዶች የታጀቡ ናቸው።
በእግሩ የሚጓዝ ነዋሪም ይሆን ጎብኚ በመዲናዋ ዞር ዞር ቢል የከተማነትን ክብርና የሰው ልጅን ነጻነት የሚያውጅ አዲስ የከተማ ልማትን በተግባር ይመለከታል።
ለወትሮው በጠባብ የእግረኛ መንገዶች፣ ለትራፊክ በማይመቹ አውራ ጎዳናዎች ትታወቅ የነበረችው መዲና፣ ዛሬ በኮሪደር ልማት አማካኝነት መልኳን እየቀየረች ትገኛለች።
ይህ ልማት የከተማዋን ውበት ከማድመቅ ባለፈ፣ የነዋሪዎቿን የዕለት ተዕለት ሕይወት ምቹ፣ ቀላልና ስሉጥ አድርጎታል።
በመዲናዋ የከተማ አኗኗርና የመንገድ አጠቃቀም ባህልም እየተቀየረ መሆኑን ያነጋገርናቸው ነዋሪዎች ይገልጻሉ።
በመዲናዋ ቀደም ባሉት ጊዜያት በእግር ለመጓዝ ምቹ መንገድ ባለመኖሩ ጉዞው አድካሚና አሰልቺ ነበር።
ዛሬ ግን ሁኔታዎች ተቀይረዋልም ነው ያሉት።
ይህም የእግር ጉዞን ማድረግ ያለውን የጤና ገፀበረከት እንድንቋደስ እያደረገን ነው ብለዋል በእግራቸው ሲጓዙ ያገኘናቸው ነዋሪዎች።
የከተማዋ ነዋሪ የሆኑት ነጋ ፍቅሬ እንደሚሉት፣ የኮሪደር ልማቱ አዲስ አበባን ለእግረኞችና ብስክሌት ለሚጠቀሙ ተጓዦች ምቹ አድርጓታል።
መንገዶቹ ለእግር ጉዞ እጅግ ምቹ ናቸው፤ በቀላሉ ለመንቀሳቀስና ለመዝናናትም አማራጭ ሆነዋል፤ ያሉት አቶ ነጋ ከቦታ ቦታ መንቀሳቀሻነት ባለፈ በየዳርቻቸው ለዓይን የሚማርኩ ሥፍራዎችን ያካተቱ መሆናቸውን አንስተዋል።
የአዲስ አበባ ልማት ስኬት ግን ከዚህም በላይ ነው፤ በአካታችነቱ የሚወደሥ ተጨባጭ ለውጥ በመዲናዋ ጎላ ብሎ ይታያል።
መምህር ጌታ ጫኔ ማየት የተሳናቸው ናቸው። ለእርሳቸው በመዲናዋ በእግር ከቦታ ቦታ መጓዝ ቀደም ሲል ትልቅ ፈተናና ስጋት ነበር። የኮሪደር ልማት ግን የእርሳቸውንና መሰል አካል ጉዳተኛ ዜጎችን ፍላጎት ታሳቢ ያደረጉ መንገዶችን እውን አድርጓል።
ይህም በተለይ ለዓይነ ሥውራን የህብረተሰብ ክፍሎች ትልቅ እፎይታን የፈጠረ ነው።
መምህር ጌታም ይህንኑ በማጠናከር ይህ ልማት ለእኛ ትልቅ ትርጉም አለው። የአካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚነት ያረጋገጠ፣ በምቾት ሳንሳቀቅ እንድንቀሳቀስ ያስቻለንና ትልቅ የመንገድ ደህንነት ስጋታችንን የቀረፈ ስራ ነው ብለዋል።
በሌላ በኩል የኮሪደር ልማቱ መዲናዋን ወደ ተሻለ የዕድገት ምዕራፍ እንዳሸጋገራት የሚናገሩት ወይዘሮ መንበረ አግዘው ናቸው።
አዲስ አበባ አሁን ለመኖርም ሆነ ለመዝናናት ተመራጭ መዲና ሆናለች ይላሉ።
አቶ ዘሩ ተገኝ በበኩላቸው የተዘረጋው መሠረተ ልማት ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል ታሳቢ ያደረገ መሆኑ አዲስ አበባ ለነዋሪዎቿ ምቹና ሰው ተኮር ልማቶች የሚከናወኑባት ከተማ እንድትሆን አድርጓታል ይላሉ።
የአዲስ አበባ የኮሪደር ልማት የአፍሪካ የዲፕሎማሲ ማዕከልነቷን በሚመጥን መልኩ ገፅታዋን ከመቀየር ባለፈ፣ ለአካል ጉዳተኞች ደህንነቱ የተጠበቀ መንገድ፣ የእግር ጉዞ ለሚያዘወትሩ ደግሞ ሰፊና ማራኪ ጎዳናን ፈጥሯል።