በጋሞ ዞን የተፈጥሮ አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ከተለያዩ ተቋማትና ግለሰቦች ድጋፍ ተደረገ - ኢዜአ አማርኛ
በጋሞ ዞን የተፈጥሮ አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ከተለያዩ ተቋማትና ግለሰቦች ድጋፍ ተደረገ
አርባ ምንጭ፤ መጋቢት 10/2018 (ኢዜአ)፦ በጋሞ ዞን በመሬት መንሸራተት አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ከተለያዩ ተቋማትና ግለሰቦች የምግብ የአልባሳትና የተለያዩ ቁሳቁሶች ድጋፍ ተደረገ።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የብልፅግና ፓርቲ ሴቶች ክንፍ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት አስተባባሪነት ከሁሉም የዞን መዋቅሮች እንዲሁም ከወላይታ ሶዶና አርባ ምንጭ ክላስተር የሴቶች ክንፍ ህብረት 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የሚገመት የቁሳቁስ ድጋፍ ተደርጓል።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሴቶች ክንፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ እቴነሽ በየነ የደረሰው ጉዳት ሁሉንም ያሳዘነ መሆኑን ተናግረዋል።
ድጋፉ ለጊዜው የሚሆን የአስቸኳይ ሰብዓዊ ምላሽ መሆኑን ገልፀው፤ ግምቱ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የሚሆን ምግብ፣ ዘይት፣ አልባሳት፣ ፍራሽና ሌሎች ቁሳቁሶችን እንዳካተተ አብራርተዋል።
የምዕራብ ዓባያ ወረዳ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት የ500 ሺህ ብር ድጋፍ ማድረጉንም የምክር ቤቱ ሰብሳቢ አቶ አብዱራህማን አዋሽ ገልጸዋል።
ድጋፉን በወረዳው ያሉ የንግዱ ማህበረሰብ አባላትን በማስተባበር የተሰበሰበ መሆኑን ገልጸው፤ ቀጣይነት ያለውን ዕገዛ ለማድረግም ማህበሩ ሀብት የማሰባሰብ ስራ እያከናወነ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
ግራንድ ጋሮ ሌግዠሪ ሆቴል የ500 ሺህ ብር ድጋፍ ሲያደርግ በአዲስ አበባ የሚገኙ የተለያዩ ግለሰቦች የ135 ሺህ ብር ድጋፍ አድርገዋል።
በጋሞ ዞን የመንግስት ረዳት ተጠሪ አቶ ተመስገን ኢዩኤል በዞኑ በጋጮ ባባና ሌሎች ወረዳዎች በደረሰው አደጋ በርካታ ቤተሰቦች መጎዳታቸውን ጠቅሰው፤ በተለይ ወላጆቻቸውን ያጡ ሕፃናትና ጧሪ ልጆቻቸውን የተነጠቁ አቅመ ደካማ አረጋውያን ለከፋ ጉዳት መዳረጋቸውን ገልጸዋል።
በዞኑ በተፈጥሮ አደጋ የተጎዱ ወገኖችን ለመደገፍ ከቅርብም ሆነ ከሩቅ እንዲሁም ከሁሉም አቅጣጫዎች በተለያዩ አካላት እየተደረገ ላለው ርብርብም ምስጋና አቅርበዋል።