መገናኛ ብዙኅን የፖለቲካ ፓርቲዎች የፖሊሲ አማራጮቻቸውን ለህዝብ የሚያስተዋውቁበት ምቹ መድረክ እየፈጠሩ ነው - ኢዜአ አማርኛ
መገናኛ ብዙኅን የፖለቲካ ፓርቲዎች የፖሊሲ አማራጮቻቸውን ለህዝብ የሚያስተዋውቁበት ምቹ መድረክ እየፈጠሩ ነው
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 10/2018 (ኢዜአ)፦ መገናኛ ብዙኅን የፖለቲካ ፓርቲዎች ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የፖሊሲ አማራጮቻቸውን ለህዝብ የሚያስተዋውቁበት ምቹ የክርክር መድረክ እየፈጠሩ መሆኑን የፖለቲካ ፓርቲ የሥራ ኃላፊዎች ገለጹ።
በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ግንቦት 24/2018 ዓ.ም ድምፅ በሚሰጥበት የዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ የመራጮች ምዝገባ ከየካቲት 28/2018 ዓ.ም ጀምሮ እየተካሄደ ይገኛል።
47 ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችም 10 ሺህ 934 ዕጩዎችን በማስመዝገብ በመገናኛ ብዙኅን አማካኝነት የምርጫ መወዳደሪያ የፖሊሲ አማራጮቻቸውን እያስተዋወቁ ነው።
የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ለኢዜአ እንዳሉት፤ ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የፉክክር ሂደት ፓርቲዎች የፖሊሲ አማራጮችን ለህዝብ የሚያስተዋውቁበት ምቹ ምኅዳር ፈጥረዋል።
መገናኛ ብዙኅን የፈጠሩት የፖሊሲ አማራጭ ማስተዋወቂያ የክርክር መድረክም ለዜጎች በነፃነት ይበጀናል ለሚሉት የፖለቲካ ፓርቲ ድምፅ መስጠት የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።
የስምረት ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ምክር ቤት አባልና የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፍ ምክትል ሰብሳቢ ጠዓመ ዓረዶም፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሀገር ጉዳይ ላይ ተመሳሳይ አቋም ሊኖራቸው ይገባል ብለዋል።
መገናኛ ብዙኅንም የፖለቲካ ፓርቲዎች በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የሚፎካከሩበትን የፖሊሲ አማራጭ ለህዝብ የሚያስተዋውቁበትን ምቹ የክርክር መድረክ እየፈጠሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎችም በመገናኛ ብዙኅን በተፈጠረው የፖሊሲ አማራጭ የክርክር መድረክ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅምና የህዝብን አንድነት ማዕከል በማድረግ ክርክራቸውን ማካሄድ እንደሚኖርባቸው ገልጸዋል።
ስምረት ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ በዜጎች መካከል አሰባሳቢና የጋራ ትርክት ለመገንባት የበኩሉን ሚና እንደሚወጣ ጠቅሰው፤ በቀጣይም ለጠንካራ ሀገረ መንግስት ግንባታ በትብብር መስራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዲሞክራቲክ ሕብረት ፓርቲ የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ ሳሙኤል ብርሀኑ በበኩላቸው፤ የምርጫ ሂደት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅምና በህዝብ አንድነት ላይ እንቅፋት መሆን የለበትም ብለዋል።
በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የሚፎካከሩ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ቅቡልነት ያለው ጠንካራ መንግስት መመስረት የሚያስችል ምክንያታዊ ክርክር ማድረግ እንደሚኖርባቸው ገልጸዋል።
ፓርቲያቸውም የተሻለች ኢትዮጵያን ለትውልድ ለማስተላለፍ እንደሚሰራም ተናግረዋል።